የወልድያ ከተማ ሠላማዊ እንቅስቃሴዋ መቀጠሉ ተገለጸ

ሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የወልድያ ከተማ እንደወትሮው ኹሉ ሠላማዊ እንቅስቃሴዋ መቀጠሉ ተገልጿል።

ወልድያ ከተማ ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ “ከወራሪው ቡድን ጋር የሚደረገው የጥምር ጦሩ ፍልሚያ አሁንም በሕዝባዊ ደጀንነት ታጅቦ እንደቀጠለ ነው።” ያለ ሲሆን፤ የወልድያ፣ የሐብሩ እና የሌሎችም ወረዳዎች ወታደራዊ ስልጠና የወሰደ ኹሉ ጥምር ጦሩ ጋር ለመቀላቀል ወደ ግንባር እየዘመቱ እንደሚገኙም አስታውቋል።

በወልድያ ከተማም ከጅቡቲ ወደብ የሚነሱ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎችንም ከተለመደው ጉዟቸው ያስተጓጎላቸው ኹኔታ አለመከሰቱንም ጨምሮ ገልጿል።

የወልድያ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን አካባቢ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ከትናንት ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓም ጀምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ አስቀምጧል።

በዚህም መሰረት፤ ከተመደበው የጸጥታ ኃይል በስተቀር ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ ማንኛውም ሰው መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ለጸጥታ ሥራ ስምሪት ከተሰጠው ተሽከርካሪ ውጭ ማንኛውም ተሽከርካሪ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ መንቀሳቀስ የማይችል መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply