የወባን በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚውል 45 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ

ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የአሜሪካ የዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) እና አይካፕ ኢትዮጵያ (ICAP/Ethiopia) የኢትዮጵያ መንግስት የወባን በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ለሚያደረገው ጥረት የሚውል 45 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርገዋል።

የህክምና ቁሳቁሶች 550 ማይክሮስኮፕ እና ሌሎች የላቦራቶሪ መመርመሪያ ቁሳቁሶች መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እንደተናገሩት፤ በጤናው ዘርፍ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሎም ለማስወገድ በሚደረገው ርብርብ የተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ ውጤታማ ሆኗል፡፡

በዕለቱም የተደረገው ድጋፍ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ በስድስት ክልሎች በሚገኙ የጤና ተቋማት የህክምና ቁሳቁሶቹ አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ ገልፀዋል፡፡

የአሜሪካ የዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ዳይሬክተር ሚስተር ቲሞቲ ስቲን በበኩላቸው፤ ባለፉት አስር ዓመታትም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የወባን በሽታ ስርጭትንና በወባ በሽታ የሚከሰተዉን ሞት በእጅጉ መቀነስ መቻሉን ገልጸው፤ ”በሽታውን በመዋጋት ረገድ ያለን አጋርነት ወደፊትም ይቀጥላል” ብለዋል።

አክለው ከተለገሱት መሳሪያዎች ውስጥ ጥቂቶቹ በግጭት ለተጎዱ የጤና ተቋማት የሚላኩና የአካባቢውን ማህበረሰብ መልሶ ለመገንባት የሚረዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአይካፕ ዳይሬክተር (ICAP/Ethiopia) ዶክተር ዘነበ መላኩ ለጤናው ዘርፍ የሚያገለግሉ 550 ማይክሮስኮፖች እና ሌሎች 50 የተለያዩ ለወባ መመርመሪያ ላብራቶሪ የሚሆኑ ግብዓቶችን በማቅረባቸው ደስተኛነታቸውን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገነኘው መረጃ አመላቷል።

The post የወባን በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚውል 45 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply