8ኛ ቀኑን በያዘው የእሳት አደጋ በምዕራብ የደኑ ክፍል መቆጣጠር ተችሏል ተብሏል።
በሰሜን ሸዋ ዞን በአንኮበር ወረዳ በወፍ ዋሻ የተፈጥሮ ጥብቅ ደን የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ፣ አሁን ላይ እሳቱን መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ መድረሱን የአንኮበር ወረዳ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታዉቋል፡፡
የወረዳዉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃለፊ አቶ ነጋሽ ተከተል ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፣ የእሳት ቃጠሎዉ ከተከሰተ 8ኛ ቀኑ እንደሆነና እሳቱን ለማጥፋት ወጣቶችና የበጎ ፍቃድ ሰዎች ርብርብ እያደረጉ ነው ብለዋል።
በዚህም አሁን ላይ በምዕራብ አቅጣጫ ያለውን የእሳት ቃጠሎ መቆጣጠር ተችሏል ነው ያሉት።
በቃጠሎው ከ 2መቶ ሄክታር በላይ የተፈጥሮ ሀብት መውደሙንና አደጋዉን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ማህበረሰቡ እየሰራ ነው ተብሏል።
ደኑ በዉስጡ በርካታ የዱር እንስሳትን በመያዙ እንስሳቱም በእሳቱ ጉዳት እንደደረሰበት ተነግሯል፡፡
የአካባቢው መልክዓ ምድር ገደላማ እና አስቸጋሪ በመሆኑ እሳቱን መቆጣጠር አለመቻሉ ሲገለፅ ነበር።
የአደጋዉን መንስዔ በተመለከተም እሳቱ ከግለሰብ ማሳ ተነስቶ ወደ ደኑ እንደተዛመተም ለማወቅ ችለናል ብለዉናል፡፡
የወፍ ዋሻ የተፈጥሮ ጥብቅ ደን በርካታ ብዝሃ ሕይወቶችን የያዘ ሲሆን፤ በተለይም በዚህ ደን ብቻ የምትገኘዋን፤ ብርቅየዋን የሶረኔ ወፍን ጨምሮ የተለያዩ አጥቢ እንስሳትንና አዕዋፋትን በዉስጡ የያዘ ሲሆን፤ 7 ቀበሌዎችንና ከ7 መቶ በላይ ሄክታር እንደሚሸፍን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በአባቱ መረቀ
መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም
Source: Link to the Post