የውጭ አገር ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ ቢሮ ከፍተው እየሰሩ መሆኑ አደጋ ፈጥሮብኛል ሲል አባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ገለጸ

ቅዳሜ ሰኔ 08 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በጥበቃ ስራ ላይ የውጭ አገር ዜጎች መሰማራታቸው በስራችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እና አደጋ እየፈጠረ ነው ሲል አባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ቅሬታውን ገለጸ።

ከ31 በላይ አባላት ያሉት አባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ከ21 ሺ በላይ ሰራኞችን ደግሞ በጥበቃ፣በጽዳት እና በቢሮ አስተዳደር ስራዎች ላይ አሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን ላለፉት ስድስት ወራት ክትትል ያደረገበትን የዘርፉ ሕገ ወጥ ድርጊት በመግለጫ አስታውቋል።

አዲስ ማለዳ ከመግለጫው እንደተረዳችው በሕግና ደንብ የማይመሩ ነዋሪነታቸውን የውጭ አገራት ያደረጉ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የዘርፉን ታማኝነት አደጋ ላይ የሚጥል ስራ እየከወኑ እንደሚገኙ ማህበሩ ባደረገው ማጣራት እንዳረጋገጠ ገልጿል።

የጥበቃ ስራ ለውጭ አገር ዜጎች ዝግ ቢሆንም የውጭ ድርጅቶች ቢሮ ተከራይተው ስራ እና ሰራተኛን በሕገ ወጥ መንገድ በማገኛኘት በህግ የተከለከለውን ስራ እየሰሩ ይገኛሉ ተብሏል።

የአባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር የሕግ ባለሞያ ማሪያ ካሳዬ እንደገልጹት በአዋጁ መሰረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው አልያም በኢትዮጵያ ቋሚ መኖሪያ የሌለው የውጭ አገር ዜጋ በጥበቃ ስራ ላይ መሰማራት እንደማይችል ተደንግጎ ይገኛል። በቀድሞው አዋጅ ቁጥር 632/2001 እና ይህንኑ አዋጅ ለማስፈጸም የወጣውን መመሪያ ወይም የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 እና ይህን መመሪያ በመተላለፍ የሰራተኞችን መብትና ደህንነት በመጣሱ ምክንያት የተሰረዘ ኤጀንሲ ሕገ ወጥ እንደሆነ ተቆጥሮ ፈቃድ እንደማያገኝ ቢገልጽም ከአዋጅ እና ደንብ ውጭ ሕገ ወጥ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አዋጅ እና እሱን ተከትሎ በወጣው ደንብ ቁጥር 474/20 አንቀጽ ንኡስ ቁጥር 29 የጥበቃ ስራ ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች የተፈቀደ መሆኑን ይደነግጋል ነገር ግን ይህንን በሚጸረር መልኩ በርካታ ድርጅቶች ወደ ስራ መግባታቸውን የአባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር አስታውቋል።

ፒ.አር.ኤስ (PRS)፣ ሲ.ጂ.ቲ (CGT) እና አማራንቴ ኢንተርናሽናል (AMARANTE international) የተባሉ የውጭ አገር ዜጎች የሚያስተዳድሯቸው ድርጅቶች ሕግና ደንብ የማይፈቅደውን ስራ በመስራት በማህበሩ አባላት ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሱ እንደሆነ ተገልጿል። ፒ.አር.ኤስ የተባለው ድርጅት አርማ ያለበት የጥበቃ ሰራተኞች የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ቢሮን እየጠበቁ እንደሚገኙም ማህበሩ አስታውቋል።

ማህበሩ አጣራሁት ባለው መረጃ እነዚህ ድርጅቶች ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ጥበቃዎችን አሰማርተው ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። እነዚህ ድርጅቶች ላሰማሯቸው ጥበቃዎች ደመወዝ ሲከፍሉ ጡረታ እንደማይቆርጡ እና ለመንግስት ተገቢውን ግብር እንደማይከፍሉ እንዲሁም የስራ ግብርም እንደማይቆርጡ ተሰምቷል።

ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚጠይቀው ስራና ሙያ የአገሪቱን ሕግና ደንብ ወደ ጎን ብለው በገቡ ተቋማት ምክንያት ስራችን ከባድ ከመሆኑም ባለፈ በስራችን ላይ ጫና አሳድረውብናል ያለው አባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር መንግስት ጉዳዩን በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው ጥሪ አቅርቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply