የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳምሶን ተክለ ሚካኤል ጉዳይ በኢትዮጽያ ለኬንያ ኤምባሲ መጥሪያ እንዲያደርስ ትዕዛዝ ተሰጠ

አርብ ግንቦት 4 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያዊው ባለሀብት ሳምሶን ተክለሚካኤል ጉዳይ በኢትዮጽያ ለሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ የመጥሪያ ደብዳቤ እንዲያደርስ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ የፍትሐብሔር ምድብ ችሎት ትዕዛዝ ሰጠ።

በኬንያ የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር ውሎ ከተሰወረ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት በላይ ባስቆጠረዉ ሳምሶን ጉዳይ፤ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በኢትዮጵያ የኬንያ ኤምባሲ ክስ ቀርቦባቸዉ እንደነበር ይታወሳል።

በዚህም መሰረት በዛሬዉ ዕለት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሽ የሆኑት የጠ/ሚ ጽሕፈት ቤት እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በችሎቱ የተገኘ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የኬንያ ኤምባሲ የክስ መጥሪያው ስላልደረሰው በችሎቱ አለመገኘቱ ተገልጿል።

በዚህም ከሳሾች በታዘዙት መሰረት ለኤምባሲ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መጥሪያ ለማድረስና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መጥሪያው እንደደረሰው ለማረጋገጥ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳጋጠማቸው የከሳሾች ጠበቃ ዶ/ር ዳባ ጩፋ ለችሎቱ ያስረዱ ሲሆን፤ ‹‹ጉዳዩን የግል በማድረግ ጭምር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጥበቃ አካላት ጭምር ዉክቢያና እንግልት›› እንደደረሰባቸዉም ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱም የከሳሽን አቤቱታ ካዳመጠ በኋላ የመጥሪያ ደብዳቤውን በክርክሩ ላይ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ወክሎ የተገኘዉ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ እንዲያደርስ፤ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትነቱ በኢትዮጵያ ለሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ መጥሪያውን እንዲሰጥ ትዕዛዝ አስተላልፏል።በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 18/2015 ከቀኑ 8 ሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን፤ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መጥሪያዉን ለኤምባሲው ስለመስጠቱ ማረጋገጫ እንዲያቀርብም አዟል።

የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተከትሎ፤ የሳምሶን ተክለሚካኤል ባለቤት ሚለን ሀለፎም ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ቃል በውሳኔው መደሰታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ‹‹ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሆነ ፍርድ ቤቱ የባለቤታቸውን ጉዳይ እንደ ዜጋ ተከታትሎ እልባት እንዲሰጥላቸውና ፍትህ እንዲረጋገጥ›› ጠይቀዋል።

ሳምሶን ተክለሚካኤል በኬንያ ናይሮቢ ባለፉት 19 ዓመታ በጋዝ ንግድ ላይ ተሰማርተው ከኬንያ ጋዝ በማምጣት ኢትዮጵያ ውስጥ በማከፋፈል ሥራ ላይ የቆዩ ሲሆን፤ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በናይሮቢ ውስጥ በአገሪቱ በጸጥታ አባሎች ታፍነው በመኪና ሲወሰዱ የሚያሳይ ቪዲዮ ከታየ በኋላ፤ እስካሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የሚታወቅ ነገር የለም።

The post የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳምሶን ተክለ ሚካኤል ጉዳይ በኢትዮጽያ ለኬንያ ኤምባሲ መጥሪያ እንዲያደርስ ትዕዛዝ ተሰጠ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply