
የዓባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው ሰከላ ከተማ የግዮን በዓል ለ5ኛ ጊዜ በዛሬው እለት በድምቀት ይከበራል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ የዓባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው ሰከላ ከተማ የሚከብረው የግዮን በዓል በዛሬው ዕለት በድምቀት ይከናወናል። የጥር ሙሽራ የሆነው አማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ የተለያዩ መንፈሳዊና ባሕላዊ መሰረት ያላቸው በዓላትን በማሳደግ የተለያዩ እሴቶችን ለቱሪዝም ሃብት ልማት ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን የክልሉ መንግስት ገልጧል። የኢትዮጵያውያን መመኪያ የሆነው የዓባይ ወንዝ በስነ ፍጥረት መጽሐፍ ከተጠቀሱት ኤዶም ገነትን ከሚያጠጡ አራት አፍላጋት አንዱ ነው። ዓባይ ከስነ ፍጥረት ተመራማሪዎች እስከ የስነ መለኮት ሊቃውንት፤ ከተፈጥሮ ሳይንስ እስከ ማኅበራዊ እድገት ምሁራን እንዲሁም ከመንፈሳውያን አበው እስከ ምስጢራዊ ማኅበራት ድረስ ዕለት ዕለት የሚዘከር የመላው ኢትዮጵያውያን ደግሞ የህዳሴያቸውና የተስፋቸው ልዩ አድማስ ነው። “የግዮን በዓል” ብለን ላለፋት አራት ዓመታት በወላዲተ ዓባይ ሰከላ ያከበርነው የቱሪዝም በዓል ዘንድሮም ለ 5ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን ዓባይ ለአማራ ክልል ሕዝብም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያዊ መንፈሳዊ ምልክቱ፣ ምግብና መጠጡ፣ ቅኔ እና ስነ ጽሑፉ ፣ ሀዘንና ደስታ፤ ቁጭትና ስስቱ ሁኖ የዘለቀ ልዩ ሃብታችን መሆኑን እንዲሁም የዘመኑ የተስፋ አድማሳችን መገለጫና ልዩ ሃብታችን መሆኑን የምንዘክርበት በዓል ሁኖ የክልላችንን የቱሪዝም እድገት የተቀላቀለ ሃብታችን መሆኑ ተመላክቷል። የጻድቁ አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ሙሽራ በሆነችው ሰከላ ተገኝተን “ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር” የተባለለት የታላቁ ግዮን/ዓባይ ወንዛችን መነሻ ምንጭ ላይ ተገኝተን የግዮንን በዓልን ስናከብር “እንችላለን” የሚለውን የኢትዮጵያውያን የሥራና የሕዳሴን መንፈስ ተላብሰን መሆን ይኖርበታል የሚል መልዕክትም ተላልፏል። በግዮን መነሻ በውቢቷ ሰከላ ተገኝቶ ጥር 13 ን ማሳለፍ ልዩ ስሜትና ደስታን የሚሰጥ በመሆኑ የማይቀርበት አንዱ የቱሪዝም ሃብት ማዕከላችን ሁኗል ሲል ያጋራው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ነው።
Source: Link to the Post