‹‹የዓድዋ ድል ጥቁሮችን ከጭቆና እና ከብዝበዛ፣ ነጮችን ደግሞ ከኢ-ሰብአዊ ድርጊታቸው ነፃ ያወጣ ታላቅ በዓል ነው›› ወጣቶች

‹‹የዓድዋ ድል ጥቁሮችን ከጭቆና እና ከብዝበዛ፣ ነጮችን ደግሞ ከኢ-ሰብአዊ ድርጊታቸው ነፃ ያወጣ ታላቅ በዓል ነው›› ወጣቶች

ባሕር ዳር: የካቲት 19/ 2013 ዓ.ም (አብመድ)ወጣቱ ትውልድ በዓድዋ የተገኘውን ድል ሀገሪቱ በምታካሂደው የድህነት ቅነሳ ሥራ መድገም እንደሚገባው ወጣቶች ተናግረዋል፡፡ አምባጊዮርጊስ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት አስማማው ነጋሽ እንደገለጸው የዓድዋ ድል ነጮች በጥቁሮች ላይ ሲያደርሱ ከነበረው ግፍ ነፃ ያወጣ እንደሆነ አንስቷል፡፡ በመሆኑም ‹‹የዓድዋ ድል ጥቁሮችን ከጭቆና እና ከብዝበዛ፣ ነጮችን ደግሞ ከኢ-ሰብዓዊ ድርጊታቸው ነፃ ያወጣ ታላቅ በዓል ነው›› ብሏል፡፡

ሌላው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ወጣት ሚኪያስ አስረስ አርበኝነት የጦር ሜዳ ጀግንነት ብቻ ሳይሆን ዜጎች በሀገራቸው ያላቸው በጎ ስሜት፣ ፍቅር፣ የሥራ ባህል፣ አክብሮት እና ተቆርቋሪነት ጭምር እንደሆነ ነግሮናል፡፡ ወጣቱ ትውልድም ቅድመ አያቶቹ በዓድዋ ላይ ያሳዩትን አንድነት ሀገሪቱ በጀመረችው የልማት እንቅስቃሴ በመድገም ታሪክ ሊሠራ እንደሚገባ መክሯል፡፡

ድህነትን፣ መሀይምነትን፣ ሙስናን እና ሌሎች ችግሮችን በመደበኛ እንቅስቃሴ ብቻ በቂ መፍትሄ ማምጣት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ ወጣቶቹ እነዚህን እና መሠል የሀገሪቱን ችግሮች በአጭር ጊዜ እና በቀላል መንገድ ለመቅረፍ ዜጎች ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ልምድና ሀብታቸውን በማስተባበር የጋራ ክንዳቸውን ሊያነሱ የሚያስችል ሀገራዊ ተቋም መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ወጣቶች የዓድዋን ድል በልማት ለመድገም የሀገራቸውን ታሪክ ማወቅ እንደሚገባቸው የገለጹት ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ቻላቸው ታረቀኝ ናቸው፡፡

ከስሜታዊነት ወጥቶ በምክንያታዊነት እና በሐሳብ ልዕልና የሚያምን ወጣት መገንባት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆን እንደሚገባውም ምሁሩ አንስተዋል፡፡

ምክንያታዊ ለመሆን ደግሞ ማወቅ፣ መመራመር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ የ300 ዓመታት ሀገረ ምስረታ ታሪክ ያላቸውን ሀገራት የደረሱበትን የስልጣኔን ማማ አሻግሮ ከማማተር ወጥቶ የ5 ሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤት የሆነችውን ሀገር በማጥናት የሀገሩን ምስጢር ማወቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሀገርን ማወቅ ሲቻል የሀገር ፍቅር ያድጋል፤ የሥራ ባሕል ይዳብራል፤ ከስሜታዊነት አውጥቶ ምክንያታዊ ያደርጋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ትክክለኛውን የሀገሩን ታሪክ በመመርመር የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ ላይ የሠሩትን ደባ ማጋለጥ እና ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ አደራ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

Source link

The post ‹‹የዓድዋ ድል ጥቁሮችን ከጭቆና እና ከብዝበዛ፣ ነጮችን ደግሞ ከኢ-ሰብአዊ ድርጊታቸው ነፃ ያወጣ ታላቅ በዓል ነው›› ወጣቶች first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.

Source: Link to the Post

Leave a Reply