የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና መልቀቂያ እንዳለፈው ዓመት ሁሉ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ ተገለጸ

በአማኑኤል ይልቃል

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና መልቀቂያ ፈተና እንደ አምናው ሁሉ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ። ለዚህ ዓመት ፈተና ምዝገባ የሚካሄደው፤ ከመጪው ረቡዕ መጋቢት 20 እስከ ሚያዝያ 15፤ 2015 እንደሆነም አገልግሎቱ ገልጿል። 

የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ይህንን ያስታወቀው፤ የ2015 የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባን አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 18 በሰጠው መግለጫ ነው። የዘንድሮው ፈተና የሚሰጥበት ጊዜ የሚወሰነው፤ ለአንድ ወር ገደማ ከሚቆየው የተማሪዎች ምዝገባ መጠናቀቅ በኋላ መሆኑን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እሸቱ ከበደ በዛሬው መግለጫ ላይ ተናግረዋል።  

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አንድ ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች በመደበኛ እና በግል ለፈተናው ሊቀርቡ ይችላሉ ተብሎ እንደሚገመት በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። ፈተናውን ይወስዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተማሪዎች ውስጥ 850 ሺህ የሚሆኑት መደበኛ እንደሚሆኑም ተገምቷል። ይሁንና ትክክለኛውን ቁጥር መናገር የሚቻለው ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑን የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ አስረድተዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የተሰጠውን የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና የተፈተኑት፤ 900 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ነበሩ። ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 18፤ 2015 የተሰጠውን ይህን ፈተና፤ የማህበራዊ ሳይንስ እና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት እንዲወስዱ መደረጉ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

The post የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና መልቀቂያ እንዳለፈው ዓመት ሁሉ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ ተገለጸ appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply