የዚህን ግራዋ ዘመን መጨረሻ አይቼ፤ ከወዳጆቼ ሁሉ አቆራረጠኝ እኮ! – ነፃነት ዘለቀ

ነፃነት ዘለቀ ([email protected])

ይህን ዘመን ዝም ካሉት ሁላችንም በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት ተቆራርጠን መቅረታችን ነው፡፡ ለደቂቃዎች ብንጠፋፋ ዓመት የተለያየን የምንመስል የነበርነው የዘሀበሻው ሄኖክ ዓለማየሁና እኔ እንኳን ይሄውና በቁርጥ “ከተጣላን” ድፍን አምስት ወር ተኩል ሊሆነን ምንም አልቀረንም፡፡ ይሄ ዘር የሚሉት የሰይጣን ትክል ለካንስ ይህን ያህል ወራዳና ብስብስ ኖሯል! እደግመዋለሁ – ወራዳና ብስብስ ያለ ብስብስ ነው! ወያኔን ምሥጋን ይንሳውና እንኳንስ በአካል የማንተዋወቅን የአንዲት ሀገር ዜጎች ይቅርና ይህ ዘመን እኮ አባትንና ልጅን፣ እናትንና ልጅን እኮ በዘር ምክንያት አባልቷል፤ አለያይቷል – አሁን እዚህ ማስታወሱ ተገቢና ገምቢ አይደለም እንጂ – ወያኔ በገባ ሰሞን – በዘረኝነት የወረት ፍቅር ያበደች አንዲት ትግሬ ከአንድ ወሎዬ አማራ የወለደችውን ሕጻን ሽንት ቤት ውስጥ ጨምራ ገድላለች – (ቀድሞ ነገር ማን ከርሱ ጋር ተኝ አላት በል)፡፡ ዘረኝነት ማለት ዐይንንም፣ ኅሊናንም፣ አእምሮንም፣ በጥቅሉ ሁለመናን የሚያሣውር መጥፎ በሽታ ነው –  በኔ ግምትና የእስካሁን ግንዛቤ ይህ በሽታ መድኃኒቱ ሞት ወይም በአንዳንዶች ላይ እንዳስተዋልኩት በእርጅና ዘመን አካባቢ ሊመጣ የሚችል ጸጸት ብቻ ነው – የጸጸት ዋጋ ደግሞ ትንሽ ነው ወይም ከናካቴው ላይኖረውም ይችላል፡፡ “ባልገጨሁት ባልሞተ” ብትል መግጨትህንም ገጭተህ መግደልህንም ስለማያስቀረው ጸጸትህ ከንቱ ነው፡፡ … ፍቅር በበዛበት ጠብም ትበዛለች … ወንድሜ ሄኖክ ወያኔ ትግሬዎችን ጥምብ እርኩሳቸውን ሳወጣ፣ የክት ስድቤንና ትችቴን ከየኮረጆየ ያለአንዳች ስስት እየመዠረጥኩ በነገር ጦር እንዳይሸጡ እንዳይለወጡ አድርጌ ስወርፍ ከአፌ እየነጠቀ በድረገጹ ይለጥፍ እንዳልነበር ዛሬ የነካውን እንጃ እንደ አብርሃ በላይና እንደነስም አይጠሬ አንዳንድ ሞገደኛ “የዴሞክራሲ ጠበቃ ሚዲያዎች” አሽቀንጥሮ ጣለኝ – ስጠረጥር ግን ይህ አዝማሚያ የተከሰተው ከነዚህ አሥርና ዘጠኝ ወራት ወዲህ በመጣብን አዲስ የዘረኝነት ልምሻ መሆን አለበት – ይቺ “ትንሽ ሥጋ እንደመርፌ ትወጋ” የሚሏት ነገር ኢትዮጵያ ላይ ድንኳኗን ደኩና እየተጫወተችብን ናት – ትናንት በውስጥ ተደብቆ የነበረ dormant volcano of racism ዛሬ እየወጣ active volcano of ethnicity ይሆንና በብርቱ ያስቸግረን ይዟል፡፡ በዚህች ደዌ እየተለከፈ ስንቱ ትልቅ ሰው ትንሽ ሆነ መሰላችሁ! የምትገርም ማግኔት ናት ወንድሞቼ፡፡ እኔን ቀልበቢስ ሞነጫጫሪውን ብቻ ሳይሆን ግርማ ካሣና መስከረም አበራን የመሰሉ ግሩም ጸሐፊዎችን ሁሉ ጥርቅም አድርጎ በ15 ነጥብ 9 ቁጥር ምስማር ዘግቷቸዋል፡፡ እስካሁን ያወጣልን የነበረው እርሱ የሚፈልገው ሀገራዊ ምስል እስኪከሰት እንደመናጆ ቆጥሮን ነበር ማለት ነው፡፡ ይሁን፡፡ ይህም ተራውን ጠብቆ ያልፋል፡፡ “ያልፋል” ብለን ያላለፈ ባለመኖሩ በዚህ አቋምም አናፍርም፡፡ ደግሞም ሰው ነውና አይፈረድበትም፡፡ በወዳጅነታችን የምንቀጥልበት ሌላ አዲስ ዘመን መምጣቱ ስለማይቀር ልፋቱን ሁሉ በነዚህ አሥር ወሮች ምክንያት አንሰርዝም፡፡ የሆነውንና እየሆነ ያለውን መናገር ግን አስፈላጊና ተገቢም ነው፡፡ መተፋፈር የለም፡፡ ለምኑ ተብሎ?

እንደአጠቃላይ አውነት ከሆነ ጆሮዋችን መስማት የሚፈልገውን ብቻ እንዲሰማ ካደረግን፣ ዐይናችን ማየት የሚፈልገውን ብቻ እንዲያይ ከፈቀድን፣ አንጎላችን ማሰብ የምንፈልገውን ብቻ እንዲያስብ ካስገደድንና መሬት ላይ የፈጠጠውን እውነት ከካድን የሁለት ጌቶች ባርያ ሆን፡፡ እንደፈረንጆቹም በ double standard አራማጅነት ታወቅን፡፡ ለሆዳችን አደርን፡፡ እውነትን ጠላን፡፡ ለሚጠፋ ነገር ሰገድን፡፡ ….

በነገራችን ላይ ዘረኝነትና የፍየል ሥጋ አንድ ናቸው፡፡

የፍየል ሥጋ ሁሉም ሰው እኩል አይመገበውም፡፡ በሽተኞች ይጠነቀቃሉ፡፡ ምክንያቱም የፍየል ሥጋ የሚበላ ሰው የውስጥ ህመሙን ሁሉ ይበረብረውና ገሃድ ያወጣበታል – ፍየል የማትበላው ነገር ስለሌላት – ይገርማችኋል እባብን ጭምር – ይህ ነገር ከዚያ ይመነጫል የሚሉ አሉ – በሌላም በኩል ፍየልን ከሰይጣን ጋር ስለሚያመሳስሏት ከዚያም አኳያ የሚያያይዙት ወገኖች አሉ – ብቻ የፍየል ሥጋ የተደበቀን በሽታ ሳይቀር ይቀሰቅሳል፡፡፡ ስለዚህም የፍየልን ሥጋ የሚበላ ሰው የሠራ አካላቱ ጤና መሆኑን መፈተሸ አለበት፡፡ አለበለዚያ ጠቅሞ ላይጠቅመው ነገረኛ ሥጋ በልቶ ለበሽታ ሊዳረግ ይችላል – እንደኔ አነሳስ ለትዝትብም፡፡ ፖለቲካችንም የፍየል ሥጋ ሆና! ሆ!

አዎ፣ “የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ” ነው ነገሩ፡፡ አዎ፣ “ያንተ ልጅ የኔን ልጅ መትቶት ከሆነ ምች ይምታው፤ የኔ ልጅ ያንተን ልጅ መትቶት ከሆነ ግን መቼም…” እንዲሉ ነው ነገሩ፡፡ አዎ፣ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነው” አካሄዳችን ሁሉ፡፡ አዎ፣ “የኔ ባል ካንቺ ባል ይበልጣልና ሽሮ አበድሪኝ” እንዲሉ ነው እማዎች፡፡ በርግጥ ምን ዓይነት የዘመን ሙጣጭ ውስጥ ገባን? እንዲህ ፍርክስክሳችን የወጣው የዱሮ አባት እናቶቻችን እንዴት አድርገው ፈጣሪን ቢያስቀይሙት ይሆን?…

አብርሃ በላይ ስለትግሬ በጨረፍታም ቢሆን ከነካህ ጽሑፍህን የጎሪጥ ያይብሃል  – መለጠፉ ይቅርና፡፡ ግንቦት ሰባትንና የወቅቱን ፖለቲካ ከነቀፍክ ወይም እየሆነ ያለውን ከተነፈስክ ኢካድፍ ከንፈሩን ይነክስብሃል – መለጠፉን ተወውና፡፡ ኦሮሞንና በፊንፊኔ ፍቅር ያበዱትን እነታከለ ኡማን መንካት አይደለም አሉታዊ በሆነ መንገድ በተዛዋሪም ቢሆን ጠቀስ ካደረግህ ዘሀበሻ ጀርባውን ይሰጥሃል፡፡ አማራን ከነካህ የአማራነት ፍቅር ከኢትዮጵዊነትና ከሰውነት ደረጃ የሚበልጥባቸው አዲስ ግልብጦች ይፎክሩብሃል (ስላልተነሳሁበት እንጂ አማራን ሊነገር የሚሰቀጥጥ መስዋዕትነት ከከፈለበት ኢትዮጵያዊነት ለመለየት የሚደረገውን ጥረት በአዲስ ወያኔነት እንደምፈርጀው በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እወዳለሁ፤ አያዋጣም፤ አማራን የጎሣ ከረጢት ውስጥ መክተት የማይቻል መሆኑን ብረዳም ሙከራው ግን ጥቂቶችንም ቢሆን ማሳቱና ማሳሳቱ አይቀርምና በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ይደረግ)፡፡ ሕወሓትን ከነካህ – ያው አንዴውኑ ተነክቶና ተነካክቶ መዘረሩ ወይም የተዘረረ መምሰሉ በጄ እንጂ – ምድረ ወያኔ በየአይጋፎረሙና በየትግራይኦንላይኑ ይንጫጫብሃል፡፡ ሁሉንም በአንዴ ማስደሰት ዶሞ አትችልም፡፡ ጨለማንና ብርሃንን ለማቀላቀል የሞከረችው ብቸኛዋ ፃዲቅ ሴት ክርስቶስ ሠምራ ናት፡፡ ሰይጣንን ከእግዚአብሔር ላስታርቅ ብላ ስትነሳ – እርሱም ሀሰት ይሁን እውነት አላውቅም፡፡ በኛ ሁኔታ ግን አንዱን ስታወደስ ሌላው ያበሻቅጥሃል፤ አንዱን ድርጅት ስትሄስ ነፈዝ ደጋፊው በስድብ ያጥረገርግሃል፡፡ ተቸገርነ፡፡ No politics of any nation on this bloody planet is more polarized than that of ours now. በለበጣ የሚያስቀውና እጅጉን የሚገርመው ደ’ሞ ሁሉም እየተነሣ “ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲ” እያለ በዴሞክራሲ ስም ሲቀልድ ቅንጣት አያፍርም፡፡ ቃሊቱን የቃቃ መጫወቻ አደረጓት፡፡ ዴሞክራሲ ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ እንዳልሆነ የምዕራቡንና የአውሮፓን ዴሞክራሲ በማየት መረዳት ይቻላል፡፡

ለነገሩ ዴሞክራሲ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ አይችልም፡፡ ምን ቅብጥ አድርጎት? ዱሮም ዱሮ ነን – አሁንማ አንድ ሁለት ቃል ከመነጋገራችን “አሃ! ከምዚ ዝብለኒ ትግራዋይ ስለዝሆንኩ እምበር…?”፣ “አሃ፣ እንዲህ የሚለኝ አማራ ስለሆንኩ አይዶል እንዴ…?”፣ “አካሲሚቲ! ሲላ ኦሮሞ ታኤቲ …?” እየተባባልን ከእንስሳትም ባሕርይ በወረደና እጅግ ባፈነገጠ ሁኔታ እየተመነቃቀርን እንገኛለን፡፡ መልካምን ነገር በባዶ መሬት ቢመኙት ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡ አታሟርትብን የሚለኝ ካለ እርሱ ማኅበረሰብኣዊ እውነቱን እንዳያይ ሌሎች ሰዎች ጋርደውበት ወይም ቁሣዊ ሕይወቱ በቦሌና በባሌ ተመቻችቶለት በተመሳስሎ የድሎት ግርዶሽ ዐይኑ የተሸፈነበተ ግልብ ወገን ነው፡፡ እንጂ ሀገራችን በአሁኑ ቅጽበት ቤንዚን ተርከፍክፎበት ክብሪት የተጫረበት ደን መሆኗን ለመረዳት ሌላው ቀርቶ የታከለ ኡማ መንግሥት በአሁኑ ወቅት የሚሠራቸውን አዲስ አበባን በአዲሱ ቋንቋ oromize የማድረግ የ24/7 አጣዳፊ ተግባር መታዘብ ከበቂ በላይ ነው፡፡ ደግነቱ ግን ይህም ልክ እንደወያኔዎቹ ሁሉ ብዙ አይዘልቅም፡፡ የነዚህም ዕኩይ ተግባር ወረት በአጭር ጊዜ ይቀጫል፡፡ ኢትዮጵያን እየጠበቃት ያለውን ኃይል ያለመረዳት ችግር ነው ሰዎች ወደዚህ ዓይነት ብልጥነትን ማዕከል ያደረገ ጅልነት እየከተታቸው የሚገኘው – ከወያኔ የማይማር መቼም የመጨረሻው ደንቆሮ መሆን አለበት፡፡ እንጂ መለስ ዜናዊና ስብሃት ነጋ ከዓለም አቀፉ የሤረኞች ኅቡዕ ኃይል ጋር ተባብረው ማጥፋት ያልቻሏትን ሀገር ዛሬ ጃዋርና ታከለ ያጠፏታል ብሎ ማሰብ በትንሹ የዋህነት ነው – ብዙ ቡልሃ አለ – ኢትዮጵያን ከደራጎኑ የወያ ፈርዖናዊ አገዛዝ ነፃ ያወጣው ቄሮና አቢይ ወይም እነጃዋር ናቸው ብሎ የሚያምን ብዙ ጅል አለ – ይገርመኛል፡፡ እነዚህ ከማን አንሼዎች የሚከናቱት ክፍተት ያገኙ መስሏቸው ነው፡፡ ወያኔም እኮ ይህን መሰል ክፍተት ነው የተጠቀመችው፡፡ ከላይ የተላከው በአካል እስኪከሰት እንዲህ ያለ የሽግግር ሁከት የሚጠበቅና ያለም ነው፡፡

እርግጥ ነው – እንዲህ ያለው አካሄድ የተወሰነ ጉዳት ላልተወሰነ ጊዜ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ሰዎች መፈናቀላቸውና ሀብትና ንብረት ማጣታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ በሀገረ አሜሪካ – ሰለጠነ በሚባለው ዓለም ውስጥ አምስት ዓመት ተኑሮ ስንትና ስንት ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት ማፍራትና ከፕሬዝደንትነት ቦታ ውጪ – እርሱም አዚያው መወለድን ስለሚጠይቅ እንጂ በቀለምና በዘር አይደለም – ከዚህ የኃላፊነት ሥፍራ ውጪ ባሉ የሥልጣን ቦታዎች ተመርጦ ወይ ተመድቦ ማገልገል በሚቻልበት ሁኔታ እኔ 40 ዓመት በኖርኩባት ከተማ መጤ ከተባልኩ በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ መመዝገብና የወደፊቷ ዓለማችን መሣቂያነት መብቃት አለበት – አሁንማ መሣቂያ መች ጠፋና – ሞልቶ! … ዶሮ መሬት ስትጭር ብዙ ነገር ታወጣለች – ስለዚህ ብዙ መጫር ላይኖርባት ነው፤ “በቀላሉ ጭራ መኖር ስትችል ለምንስ ብዙ መጫር አስፈለጋት?” ብሎ መጠየቅም ሞኝነት አይደለም፡፡ ለማንኛውም ግን ይቺ የወያኔ አካሄድ ለማንም አትበጅም፡፡ የመጨረሻውና የተኛው… የማን ዘበራቂ ነኝ እናንተዬ፡፡ ኤጭ! ይሄ ጉደኛ ዘመን በኔው ዕድሜ ይድረስ? ለማንኛውም የሁሉም ነገድ ልባሞች ይችን ጊዜ በጥንቃቄ ያዟት፡፡

“ፍቅር ያዘኝ ብለህ አትበል ደምበር ገተር፤

እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አ’ርጎን ነበር” ብላ አቀንቅናለች ‹አብረኸት ባራኺ› ነፍሷን ይማረውና፡፡ (ሞታለች እንዴ ግን?)

ዴሞክራሲና ሃሳብን በነፃነት መግለጽ እንግዲህ እንደዚህ ነው፡፡ ለራስህ ሲሆን እስከፑንት – ለሌሎች ሲሆን አንድያውን ጥርቅም! ወይም በመለኪያና በመቁነን – እንደገዳም ሬሽን፡፡ አየ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን! ከስደትና በስደት እንኳን ምንም የማንማር ግትሮች፡፡

እኔ ደግሞ እላለሁ – አንድ ሰው የሚናገረው እውነት እስከሆነ ድረስ – እውነት ባይሆን እንኳን በተሳሳተ መረጃ ምክንያት የመሰለውን ግን ለጦርነትና ለዐመፅ የማይጋብዝ ሃሳብ እስከተናገረ ወይ እስከጻፈ ድረስ ሃሳብን በሃሳብ መሞገት እንጂ ማፈን ወይም ባልተመጣጠነ መሣሪያ ወግቶ በሚገኝ ድል መቦረቅ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ባደጉ ሀገሮች መሪዎቻቸውን በጦጣና በዝንጀሮ፣ ሲፈልጉ በውሻና በጉማሬ እየመሰሉ ቢያወጡ ማንም ዝምባቸውን እሽ የሚላቸው የለም (እኛ ጋ እኮ ወዲያውኑ ማምለክ ወይም በሰይጣንነት ፈርጆ ማውገዝ እንጂ ማስተዋል ብሎ ነገር አልፈጠረብንም፤ አሁን አቢይን በትችት መልክ ተስቶህ ወይም አምነህበት ትንሽ ብትነካ … ኧሯሯ… ይወርዱብሃልኝ፡፡) ባደጉ ሀገሮች ሰዎች እላፊ ቢናገሩ እንኳን አበዱ ተብለው በአንባቢዎች ይተቻሉ እንጂ እነሱን እየተከተለ ጊዜውን የሚያጠፋ መንግሥታዊም ሆነ ግላዊ አካል ያለ አይመስለኝም፡፡ የኛ ሀገር እኮ የተለዬ ነው፡፡ ሁሉም ስላንተ እርሱ ነው የሚያውቅልህ፡፡ ሁሉም ምርጫህን እርሱ ነው የሚወስንልህ፡፡ የቤቢሲተሩ (babysitter) ብዛት ከቁጥር በላይ ነው፡፡ መንግሥት  ቤቢሲተር ነው፤ ተቃዋሚዎች ቤቢሲተር ናቸው፤ ጋዜጠኞች ቤቢሲተር ናቸው፤ ባለድረገፆች ቤቢሲተር ናቸው፤ ሁሉም እንዳልል ጥቂቶች ስለሚጨፈለቁብኝ ፈርቼ እንጂ አብዛኛው የግልም ሆነ የመንግሥት ሚዲያ ቤቢሲተር ነው፤ ታዋቂ ግለሰቦች ቤቢሲተር ናቸው፤ ነጋዴው ቤቢሰተር ነው፤ ሀኪሙ ቤቢሲተር ነው (ራስህን አሞህ እግርህን ሊያክምህ የሚጎነበስ እኮ እኮ አለ – ብትነግረውም በትዕቢት ተወጥሮ የማይሰማህ)፤ … እኛ እንግዲህ የት እንግባ? የዚህ ሁኔታ ምንጭ ሕዝብን መናቅ ነው፤ ሕዝብን ምርጫ እንደሌለው ባዶ ጭንቅላት (ነጮቹ ታቡላራዛ የሚሉት) እንደሆነ አድርጎ የመቁጠርና ራስን ሰማየ ሰማያት የመስቀል ልክፍት ነው፡፡ የሚገርም ሀገራዊ ቋሚ ልክፍት፡፡ ሕዝብ አያውቅም ካልን እንዲያውቅ መንገዶችን ማመቻቸት ነው፤ ትምህርትን በጥራት መስጠት ነው፤ የንቃተ ኅሊና ማሳደጊያ ማዕከላትን ማቋቋምና በሁሉም ረገድ መደገፍ ነው፡፡ ሕዝብን የማብቃት ሥራ መሥራት ነው፡፡ ራስንም ከሙስናና ከዘረኝነት ማጽዳት፣ በዕውቀትና ችሎታም ማነጽ ነው፡፡ …. በዚህ መልክ መቀጠሉ ግን ወደ ገደል መጓዝ ነው፡፡

እንግዲህ ስለኛ የሚገርም ጉዳይ ይችን ታህል ከተነፈስኩ በቃኝ፡፡ ግን ከጀርባቸውም ሆነ ከፊት ለፊታቸው ምንም ዓይነት ቁስል የሌለባቸው (የሚመስሉኝ – ቢያንስ)፣ ከፊትም ሆነ ከኋላ ገራፊና ተቆጣጣሪ ያልተመደበባቸው፣ ለእንጀራ ሲሉ የዴሞክራሲን ባህል እንደሸቀጥ ዋጋ የማያወጡና የማያወርዱ፣ በዘር ልክፍትም የማይሰቃዩ፣ ሙያን በእንጀራ የማይለውጡ፣ ዴምራሲን ለመተሻሻነትና ለመሞዳሞጃነት ወይም ለመመሳሰል ሲሉ የቃሉን ፍቺ በመዘንጋት ራሳቸውን ለትዝብት የማይዳርጉ እነ እንትናን የመሰሉ ግለሰቦችና ድረገፆች እንዳሉ በዚህ አጋጣሚ መናገር ተገቢ ነው – ማስታወቂያ እንዳይመስልብኝ ለጊዜው ስማቸውን መናገር አልፈለግም፡፡ እንጂ ወላድ በድባብ ትሂድ አሉ፡፡ በነገው ቀን የማያሳፍሩን ለፈይሣ የማይሉ፣ ለአምባቸው የማይሉ፣ ለፍትዊ የማይሉ፣ ዘበርጋ ሲነሳ ወከክ የማይሉ፣ ግምብወግሽ ስትጠራ ፊታቸውን ኮሶ የማያስመሰሉ፣ …. ጥቂትም ቢሆኑ ለኅሊናቸው ያደሩ አሉን – በምድረ በዳው ጉዟችን ጉልበታችን እንዳይዝል የሚያበረታቱንና ተስፋ የሚሆኑን፤ በበረሃማው ዝምዝም መንገዳችን ምንጭ ሆነው የውኃ ጥማታችንን የሚያስታግሱልን – በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የብርሃን መቅረዝ የሚሆኑን እጅግ ጥቂት ሻማዎች አሉን – እግዚአብሔር እነሱን ያብዛልን፤ ከሀሰተኛና አስመሳይ ነቢያት፣ ጊዜ እየጠበቁ በዚህ ወይ በዚያ ምክንያት ከሚከዱን ግን ይጠብቀን፡፡ የዛሬው ማፈሪያ ታሪካችን በነገው ዕለት ሲለወጥ – የድል አጥቢያ አርበኛው ቢበዛና በዚያም ሥርዓት እንደእስስት ዐመልን ቀይሮ ማስቸገሩን ቢቀጥልም – ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ተገቢ ክብራቸውን ያገኛሉ፡፡ ዛሬ የተጎሳቆሉ፣ ኑሮና ሕይወታቸውን ለማሻሻል ሲሉ ሕዝባዊውን የሀገር ትንሣኤ ዓላማና ትግል እንደኢሣው በጭብጥ ምሥር ያልለወጡ ወገኖቻችን ይህችን ሀገር ከፈጣሪ እጅ ተረክበው እንደገና የዓለም ቁንጮ ያደርጓታል፡፡ ከሥር የነበረ ቁንጮ ቢሆን ያስደስታል የፈጣሪን ፍርድ ትክክለኝነትም ያሳያል  እንጂ አያስከፋም፤ ትዕቢተኛና ትምክህተኛም አያስብልም – የቀኝ ኋላ ዙር አንዱ ትርጉምም ይሄው ነውና! መጽሐፉስ “ፊተኞች ኋለኞች፤ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ” ይል የለምን?

Leave a Reply