የዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎቿ በጅምላ ተይዘዋል ስለተባሉት የትግራይ ተወላጆች መግለጫ አወጡ

https://gdb.voanews.com/CE122D37-6488-4EF3-95C1-7B93251077F8_w800_h450.jpg

የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ያለምንም ክስ በትውልድ ማንነታቸው ብቻ ሰብስቦ ማሰሩን እንቃወማለን፣ ባለፈው ጥቅምት 23 በመንግሥት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ለዚህ የጅምላ እስር በቂ ምክንያት አይሆንም ሲሉ ስድስት ሃገሮች ባወጡት የጋራ መግለጫቸው አስታወቁ፡፡

በጋራ መግለጫው ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት ሃገሮች አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ ኔዘርላንድ፣ እንግሊዝና፣ ዩናይትድ ስቴትስ መሆናቸውን በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል የወጣው መግለጫቸው ያስረዳል፡፡

6ቱ ሃገሮች በመግለጫቸው፣ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቀሳውስትን ጨምሮ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ፣ አረጋውያን እናቶችና ህጻናት እየታሰሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ያውጡት ዘገባዎች ያመለክታሉ ብለዋል፡፡

ግለሰቦች ምንም ክስ ሳይመስረትባቸውና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ሰብአዊ ባልሆነ ሁኔታ ታስረው ይገኛሉ ሲሉም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡

ሃገሮቹ በመግለጫቸው የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነርና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከግጭቱ ጋር ተያይዘው የተፈጸሙ ሰብአዊና የጾታ ጥቃቶች በእጅጉ ያሳስቡናል ብለዋል፡፡

ለግጭቱ ምንም ዓይነት ወታደራዊ መፍትሄ እንደሌለው ግልጽ ነው ያለው መግለጫቸው፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ባለፈው፣ ዛሬም ይሁን ለወደፊቱ፣ የሚደርሰውን የሰብአዊ ጥቃት እናወግዛለን ፣በማለት ሁሉም ወገኖች ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ለማድረግ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲደራደሩ በድጋሚ እናሳስባለን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሁሉን አካታች የሆነ አገራዊ የፖለቲካ መግባባት እንዲፈጥሩ ጥሪ ያደረጉ ሲሆን ለሰብአዊ መብት ጥሰት ኃላፊነት ያለባቸውም ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብለዋል ሃገራቱ በመግለጫቸው፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply