የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚካሄደው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳስቦኛል አለ

በምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች በትግራይ ተወላጆች ላይ በአማራ የፀጥታ ኃይሎች ጅምላ እሥር ግድያና መፈናቀል እንደተፈፀመ የሚናገረው “ያልተረጋገጠ” ያለው አዲስ ሪፖርት ዩናይትድ ስቴትስን በእጅጉ ያሳሰባት መሆኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ዛሬ ገልጿል።

ካለፈው ዓመት ኅዳር ወዲህ ከምዕራብ ትግራይ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች በኃይል መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስታወቁን መሥሪያ ቤቱ አስታውሶ

“ሁሉም የአማራ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀምን ጥቃት እንዲያወግዙ” እንጠይቃለን ብሏል። “የኤርትራ ኃይሎች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ሲል አክሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት አቤቱታዎቹን እንዲመረምርና ጥቃት ፈፃሚዎችን በተጠያቂነት እንዲይዝ፣ ሁሉን አሳታፊ የሆነ ግልፅ ምርመራ እንዲያደርግ፣ ሁከቱ እንዲቆም፣ ታጣቂ ወገኖች ሁሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያቆሙ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ባልተገደበ ሁኔታ እንዲደርስ መሥሪያ ቤቱ ጠይቋል።

“ሁሉን አካታች ውይይት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲጀመርም ጥሪያችንን በድጋሚ እናሰማለን” ብሏል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት “የፈጠራ ቅጥፈቶች ለጊዜው ቢያደናግሩም እውነት የመሆን ዐቅም ግን የላቸውም” በሚል ርዕስ ማምሻውን ባወጣው ሰሞኑን ምዕራብ ትግራይ ላይ ተፈፅመዋል ተብሎ በሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋማት የወጣውን ሪፖርትና የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች “የፈጠራ ክሥ” ሲል አስተባባሏል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply