
የይልማና ዴንሳ ወረዳ የብልጽግና ስርዓት አገልጋዮች አዴት ላይ በከፈቱት ተኩስ ሁለት ፋኖዎችንና አንድ ሲቪል ቆሰሉ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ሀምሌ 14/2015 ዓ/ም_አዲስ አበባ ኢትዮጵያ በምዕራብ ጎጃም ዞን የይልማና ዴንሳ ወረዳ የብልጽግና ስርዓት አገልጋዮች የወረዳው ፋኖዎች ሀርዝባችን የህልውና ፈተና ውስጥ በገባበት በአሁኑ ሰዓት ትጥቅ እና ስልጠና ልንከለከል አይገባም በማለት አዴት ላይ ምክክር አድርገዋል። ሀምሌ 14/2015 ከይልማና ዴንሳ የጸጥታ አመራሮች ጋር በተወካይ ሽማግሌዎች በኩል ጠዋት ላይ ለመምከር የሞከሩ ቢሆንም አመራሮቹ “አዋጅ ስላለ መሳሪያ ይዛችሁ እንድትንቀሳቀሱ እና ስልጠና እንድታካሂዱ አንፈቅድም” የሚል ምላሽ ስለመስጠታቸው የአሚማ ምንጮች ጠቁመዋል። ሰላማዊ ጥያቄ አቅርበው የተከለከሉት ፋኖዎችም በሰልፍ ከከተማ እየወጡ ሳለ በክህደት ቆረጣ ባደረጉ የአገዛዙ ተልዕኮ ፈጻሚ የሆኑ ውስን የፖሊስ አባላት ቀድመው ቦታ በመያዝ ጥይት ተኩሰው ሁለት ፋኖዎችን አቁስለዋል፤ ከማን እንደሆነ ባይታወቅም ሌላ አንድ የከተማው ነዋሪ ደግሞ በተባራሪ ጥይት መቁሰሉ ተሰምቷል። አንደኛው ፋኖ ሪፈር ተብሎ ወደ ባህር ዳር ስለመላኩ የአሚማ ምንጮች ተናግረዋል። የአባላቱን መመታት ተከትሎ ቦምብ የተጣለ ቢሆንም የደረሰ ጉዳት የለም ተብሏል። የቆሰሉ ፋኖዎች መኖራቸውን ተከትሎ በሁኔታው የተደናገጡት የይልማና ዴንሳ ወረዳ አመራሮች ለፋኖዎች ሽማግሌ እየላኩ ስለመሆኑ ታውቋል። “የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል” በበኩሉ ሐምሌ 14/2015 ዓ.ም “የታጠቁ ኃይሎች” ብሎ በመጥራት፣ እነዚህ አካላትም ጥያቄ ስለማቅረባቸውና ስለመከልከሉ፤ በክልከላው ባለመስማማት ተኩስ ስለመክፈታቸውና ጉዳት ስለመድረሱ ጠቁሟል። ትጥቅ ይዘን እንቀሳቀስ በማለታቸው እና በክልከላው ባለመስማማታቸው “አፍራሽ ሀሳብ ያላቸው ቡድኖች” ሲል በመጥራት ነዋሪው ፍላጎታቸውን በመረዳት የተዘጉ መንገዶችን እንዲከፍት ጠይቋል። አሚማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው ለጥያቄያዎቸው ምላሹ ክልከላ መሆኑን የተረዱት ፋኖዎች ከከተማ እየወጡ ባሉበት ሁኔታ ቆረጣ አድርገው የቆዩ የፖሊስ አባላት ናቸው ቀድመው በመተኮስ ሁለት ፋኖዎች ላይ ጉዳት ያደረሱት ሲሉ ተናግረዋል።
Source: Link to the Post