You are currently viewing የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የሚሰራ የልማት ድርጅት ሊያቋቁም ነው 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የሚሰራ የልማት ድርጅት ሊያቋቁም ነው 

በሃሚድ አወል

በይፋ ከተመሰረተ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የሚሰራ የልማት ድርጅት ለማቋቋም ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ክልሉ ምርጥ ዘር የሚያቀርብ የመጀመሪያውን የልማት ድርጅት የሚያቋቁም ደንብ፤ ከአንድ ወር በፊት አጽድቆ ወደ ስራ መግባቱም ተገልጿል። 

ፌዴሬሽኑን በመቀላቀል አስራ አንደኛ የሆነው አዲሱ ክልል፤ ሊያቋቁመው ላቀደው ሁለተኛው የልማት ድርጅት ጥናት በማካሄድ ላይ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ ‘ምን አይነት የኮንስትራክሽን ሴክተር ነው የምናቋቁመው?’ የሚለውን ለመለየት ጥናት ላይ ነን። ህንጻ አለ፤ የመጠጥ ውሃ አለ፤ መንገዱም አለ። [ዘርፉ] በርከት ያለ ስለሆነ፤ ሁሉንም ሰብሰብ አድርገን አንድ ጠንካራ ተቋም ብናደራጅ የተሻለ ነው” ሲሉ አዲሱን የልማት ድርጅት ለማቋቋም የተደረሰውን ውሳኔ አስረድተዋል። 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል “በጣም ዝቅተኛ የመሰረተ ልማት ሽፋን ያለበት ነው” – የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ

“ክልላችን በጣም ዝቅተኛ የመሰረተ ልማት ሽፋን ያለበት ነው” የሚሉት ዶ/ር ነጋሽ፤ የልማት ድርጅቱ የመሰረት ልማት ግንባታ ላይ የሚያተኩር ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል። “የግል ሴክተሩ በማይሰራባቸው፣ መድረስ በማይችልባቸው እና ፍላጎት በማያሳይባቸው አካባቢዎች ላይ፤ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በመጠቀም የተሻለ የህዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄ መመለስ ይቻላል” በሚል እምነት የልማት ድርጅቱን ለማቋቋም ቅደም ዝግጅት መጀመሩን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል። 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን እየፈተኑት ካሉት ተግዳሮቶች መካከል አንዱ፤ የመሰረተ ልማት እጥረትን የማሟላት ጉዳይ እንደሆነ ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ በቦንጋ ከተማ በተከበረው የክልሉ አንደኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል ወቅት ተነስቶ ነበር። በዚሁ ክብረ በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፤ የመንገድ፣ የድልድይ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የመብራት አቅርቦት የክልሉ “ትልቅ ተግዳሮቶች” መሆናቸውን ጠቁመዋል። 

በአዲሱ ክልል የሚገኙ የመሰረት ልማቶች “በቁጥርም ይሁን በጥራት ደረጃቸውን የሚያሟሉ አይደሉም” ያሉት ዶ/ር ነጋሽ፤ “ወረዳ ከተሞች ጭምር መብራት የማያገኙበት ሁኔታ ይስተዋላል” ሲሉ በክልሉን ያለው የመሰረተ ልማት ችግር መጠነ ሰፊ መሆኑን በወቅቱ አስረድተው ነበር። በክልሉ የአስር ዓመት የልማት ፍኖተ ካርታ ሰነድ ላይ የሰፈረው መረጃም የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን ገለጻ የሚያስተጋባ ነው። በሰነዱ መሰረት፤ በክልሉ ያሉ በርካታ የገጠር ከተሞች ከዋናው የኃይል መስመር ውጭ (Off grid lines) በመሆናቸው ኤሌክትሪክ አያገኙም። 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካሉ 39 ወረዳዎች ውስጥ በአስፋልት መንገድ የተገናኙት አምስት ወረዳዎች ብቻ ናቸው

በክልሉ ካሉ 39 ወረዳዎች ውስጥ በአስፋልት መንገድ የተገናኙት አምስት ወረዳዎች ብቻ መሆናቸውን በዚሁ ሰነድ ሰፍሯል።  የክልሉ አጠቃላይ የአስፋልት መንገድ ሽፋን 385.9 ኪሎ ሜትር መሆኑም በሰነዱ ላይ ተመላክቷል። እንደ መንገድ ሁሉ፤ የክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትም “እጅግ በጣም አነስተኛ” እንደሆነ ሰነዱ ያሳያል። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ዶ/ር ነጋሽ የሚመሩት ክልል፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ከ50 በመቶ በታች ነው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያሉበትን የመሰረተ ልማት ችግሮች ለመቅረፍ “ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” የተባለለትን የልማት ድርጅት ዕውን ለማድረግ ያቀደው “በሚቀጥለው ዓመት መግቢያ አካባቢ” መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በልማት ድርጅትነት ለክልሉ የመጀመሪያው የሆነው የምርጥ ዘር ድርጅት ግን ከእቅድ እና የማቋቋሚያ ደንቡን ከማጽደቅ ተሻግሮ፤ ተቋሙን የማደራጀት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ዶ/ር ነጋሽ ገልጸዋል። 

“በክልሉ ውስጥ የሚያስፈልጉ የምርጥ ዘር አቅርቦቶችን ከገበያ እየተሻማን ከምናቀርብ፤ በዚህ ተቋም በኩል በቀላሉ የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት እናሟላለን” ሲሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የድርጅቱን መቋቋም አስፈላጊነት አብራርተዋል። “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት” የተሰኘ ስያሜ ያለው ይህ ተቋም ሶስት ዓላማዎች እንዳሉት በማቋቋሚያ ደንቡ ላይ ተቀምጧል።

ፎቶ ፋይል፦ ከኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተወሰደ

የድርጅቱ የመጀመሪያ ዓላማ፤ የተለያዩ ሰብል እና የእንስሳት መኖ ዘሮችን ማባዛት እና አዘጋጅቶ ለደንበኞች ማቅረብ ነው። ድርጅቱ ለዚህ ስራው የራሱን፣ የመንግስት እና የግል ድርጅቶችን እንዲሁም የአርሶ እና አርብቶ አደሮችን መሬት መጠቀም እንደሚችል በማቋቋሚያ ደንቡ ላይ ተደንግጓል። ሁለተኛው የድርጅቱ ዓላማ፤ አስፈላጊ የሆኑ ሰብል እና የመኖ ዘሮችን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር ወደ ክልሉ በማስገባት ለአርሶ አደሮች ማቅረብ ነው። ድርጅቱ፤ የዘር ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ተጨማሪ ዓላማም አለው። 

“የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት” ተጠሪነቱ ለርዕሰ መስተዳድር እና መስተዳድር ምክር ቤት ነው። የልማት ድርጅቱን የሚመራውን ቦርድ የሚሰበስቡት የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሆናቸውን በማቋቋሚያ ደንቡ ላይ ሰፍሯል። በ20 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል እንደተቋቋመ የተገለጸው ይህ የልማት ድርጅት፤ ወደ ምርት ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው “በዚህ ዓመት መጨረሻ” እንደሆነ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

The post የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የሚሰራ የልማት ድርጅት ሊያቋቁም ነው  appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply