
የደቡብ ጎንደር ዞን መስተዳድር እብናት ላይ የደረሰበትን ሁለንተናዊ ኪሳራ የእስቴ ፋኖዎችን በማጥቃት ለማካካስ ዝግጅት ላይ መሆኑ ተገለጸ፤ “እኛ የምንላችሁን ተልዕኮ የምትፈጽሙ ከሆነ ከደመወዛችሁ ላይ 1,500፣ አንድ ሽህ አምስት መቶ ብር እንጨምርላችኋለን” በማለት ለዘመቻው አባላትን እያዘጋጁ ነው ተብሏል። አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ሀምሌ 4/2015 ዓ/ም_ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ የደቡብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ እብናት ላይ በእነ ሻለቃ ውባንተ አባተ እና ሻለቃ ተሾመ አበባው ላይ ተኩስ በከፈተበት ወቅት የደረሰውን ሁለንተናዊ ኪሳራን በእስቴ ፋኖ ላይ በመዝመት ለመበቀል እየሰሩ ነው ሲሉ የአካባቢው ፋኖዎች ለአሚማ ተናግረዋል። “እኛ የምንላችሁን ተልዕኮ የምትፈጽሙ ከሆነ ከደመወዛችሁ ላይ 1,500፣ አንድ ሽህ አምስት መቶ ብር እንጨምርላችኋለን” በማለት ወደ ፋኖዎች ለማዝመት እና እርስ በርስ ለማዳማት ከሀምሌ 3/2015 ምሽት ጀምሮ ሲደረግ የነበረው ኃይል የማሰባሰብ እና ለስምሪት የማዘጋጀት ሂደት ተቃውሞ ገጥሞታል። በተለይም ከመካነ እዬሱስ ከተማ የተጠረነፉ የፖሊስ አባላትና አንዳንድ ሚሊሾች “ለመሆኑ የት ነው የምንሄድ?፣ ለምን ተልዕኮ?” የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው አዛዦችን ቅር ማሰኘቱና እቅዱ ከጅምሩ ስለመክሸፉ ማሳያ ስለመሆኑ ተመላክቷል። ነገር ግን ከካድሪዎች የተሰጠው ምላሽ “ወታደር በባህርይው የት ነው የምንሄድ ብሎ አይጠይቅም፤ ሂዱ ስትባሉ፤ አድርግ ስትባል ታደርጋለህ” የሚል መሆኑ አባላቱን ያበሳጨ መሆኑ ተገልጧል። በዚህም የመካነ እዬሱስ ከተማ የፖሊስ አባላትና ሚሊሾች ሀምሌ 3/2015 ምሽት ላይ ለስምሪት በተጠረነፉበት “ከፋኖዎች ጋር ከሆነ ከእነሱ ጋር እኛ መጣላት አንፈልግም፤ እኛን በትናችሁ ደግሞ እነሱን ለመበተን ከሆነ አይታሰብም!” የሚል ጠንካራ አቋም በመያዛቸው ዘመቻው ሳይሳካ ቀርቷል ተብሏል። ይሁን እንጅ ፋኖን ለመምታት ከእስቴ ገጠር ወረዳ ከየቀበሌው በማሰባሰብ ያስመጧቸውን ከልዩ ኃይል ወደ ፖሊስ ያቀላቀሏቸው አባላትን እና ሚሊሾችን በተለምዶ ቻይና በሚባል ካምፕ በማስቀመጥ አሁንም ከፋኖ ጋር ለማጋጨትና ለማዳማት ለስምሪት እያዘጋጇቸው መሆኑ ታውቋል። በዚህ ሰበብ እየፈጠሩ በገብርዬ ብርጌድ የአምባቸው ሻለቃ የፋኖ አባላትን ለመምታት በመጠርነፍ እና ስምሪት በመስጠት ሂደቱ በዋናነት እጃቸው ያለበትም:_ 1) አቶ አሸናፊ_የደቡብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ 2) ኮማንደር በለጠ ስንታዬሁ_ የእስቴ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ፣ 3) ጸጋዬ አበረ_የመካነ እዬሱስ ከተማ የጸጥታበዘርፍ ኃላፊ እና 4) ኮሎኔል ምትኩ_የእስቴ ወረዳ ሚሊሻ ጽ/ቤት ኃላፊ መሆናቸው እንዲታወቅልን ሲሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል። እስቴ ወረዳ ከፋኖዎች ትጥቅ አላግባብ ከመውሰዱ ባሻገር እንዲመለስ በሚል በዳኝነት ሂደት ላይ ያለን መሳሪያ በህገ ወጥ መንገድ እያወጡ ለአባላት መስጠታቸው ተገቢ አይደለም በሚል ቅሬታ ስለመኖሩ ለማወቅ ተችሏል። በገብርዬ ብርጌድ የአምባቸው ሻለቃ ፋኖን የሚመራው ባዬው መልካሙ አሳዬ የተባለ የአካባቢው ነዋሪ መሆኑ ተሰምቷል።
Source: Link to the Post