
የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ተማሪ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሕይወቱ አልፎ ተገኘ። የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ግንቦት 2/2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የአንደኛ ዓመት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ የነበረው አበባው ስንሻው መጸዳጃ ቤት ውስጥ ገብቶ የመግቢያውን በር በመቆለፍ በቀበቶ ራሱን አጥፍቶ መገኘቱን ዩኒቨርሲቲዉ አስታውቋል። ዩኒቨርሲቲዉ፤ ተማሪዉ እዚህ አሳዛኝ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ያበቁትን ጉዳዩች ተጨማሪ ማጣራት የሚያስፈልግ ቢሆንም፤ ‹‹ፈተና ከበደኝ›› በሚል ሲጨናነቅ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ ብሏል። ነገር ግን አዲስ ከዩንቨርስቲው ተማሪዎች የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው፤ በዩኒቨርስቲው በተደጋጋሚ ተማሪዎች ህይወታቸው አልፎ ከቀናት በኋላ የሚገኙ ሲሆን፤ ከቀናት በፊትም አንድ ተማሪ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በቅጥር ግቢው ውስጥ ተገድሎ መገኘቱ ተገልጿል። ይህ ሁኔታ በዓመቱ ሲከሰት ለአራተኛ ጊዜ ነዉም ተብሏል። ተማሪዎች በሌሊት ወደ ቤተክርስቲያን ሲወጡና ከመሸ በግቢዉ ሲንቀሳቀሱ በስለት እየተወጉ የተገደሉ ተማሪዎች መኖራቸዉንም የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ገልጸዋል። ግንቦት 2/2015 ከረፋዱ 3 ሰዓት አካባቢ የተማሪ አበባው ስንሻውን ሕልፈት ተከትሎ የተማሪዉ አስክሬን ከግቢዉ በሚወጣበት ወቅትም፤ የተቃውሞ ሰልፍ በወጡ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ታውቋል። በዚህም የመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች ተኩስና አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመው ተማሪዎች እንደበተኗቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በርካታ ተማሪዎችም በዩንቨርስቲው አጥር በኩል ዘለው ማምለጣቸው ታውቋል። የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ የተማሪዉን ህልፈት ተከትሎ የተሰማዉን ሀዘን ገልጿል ሲል አዲስ ማለዳ ዘግቧል።
Source: Link to the Post