የዴንማርክ የአየር ንብረት ሚኒስትር የአፋር ክልልን ጎበኙ

https://gdb.voanews.com/06a20000-0aff-0242-ada3-08daffc6aa6f_w800_h450.jpg

የዴንማርክ የአየር ንብረት ሚንስትር ዳን ጆርገንሰን ትናንት ረቡዕ የኢትዮጵያ የአፋር ክልልን ጎብኝተዋል፡፡ ድርቅ በተጠቃው የአፋር ክልል የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማቆም ባለፈው ህዳር የተደረሰውን ሥምምነት ተከትሎ የረድዔት እንቅስቃሴ መቀጠሉን ሮይተርስ የዓለም የምግብ ፕሮግራምን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ብዙ መቶ ሺዎች ለረሃብ ሲዳርግ ብዙ ሺዎች መገደላቸውን እና አያሌ ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውን ሮይተር አክሏል፡፡

በየቀኑ ለራሳቸው እና ለስድስት ልጆቻቸው ምግብ ሊቀበሉ ከመጠለያቸው ወደ የዓለም የምግብ ፕሮግራምን የምግብ ዕደላ ጣቢያ የሚመላለሱት ኡሮ ኮኖጆ ሙሉ በሙሉ የሚተማመኑት በሚሰጣቸው ዕርዳታ ላይ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዴንማርክ የአየር ንብረት ሚንስትር ዳን ጆርገንሰን “በተለይ የበለጸጉት ሀገሮች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አንዱ ኃላፊነታችን የካርቦን ልቀታችንን መቀነስ ነው፡፡ ይህን ሳናደርግ ስንቀር የሚሆነውን እያየን ነው የአየር ንብረት ለውጥ ህዝብን ይጎዳል፡፡ ደግሞም ጉዳቱ ወደፊት የሚመጣ ሳይሆን አሁን እየደረሰ ነው” ብለዋል፡፡

“የችግሩ መንስዔ መሆናቸው ሲነገር የቆየው የበለጸጉት ሀገሮች የበለጠ ሥራ ይጠበቅባቸዋል” ሲሉም ሚንስትሩ አሳስበዋል፡፡

“ድርቁ አብዝቶ ጎድቶናል” ያሉት ኡሮ ኮኖጆ “ላለፉት ሦስት ዓመታት ዝናብ አላየንም፤ ከብቶቻችንም ሳር አላገኙም ብዙ ከብቶች ሞተውብኛል” ብለዋል፡፡ ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply