የዶናልድ ትራምፕ አስተያየት ከአንድ የሀገር መሪ የማይጠበቅና የዓለም ዓቀፍ ህግን ያላገናዘበ ነው- የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

የዶናልድ ትራምፕ አስተያየት ከአንድ የሀገር መሪ የማይጠበቅና የዓለም ዓቀፍ ህግን ያላገናዘበ ነው- የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰጡት አስተያየት ከአንድ የሀገር መሪ የማይጠበቅና የዓለም ዓቀፍ ህግን ያላገናዘበ መሆኑን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡
ምሁራኑ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የእድገት ተስፋ ማሳያ ምልዕክት በመሆኑ በውጪ ሀገራት ተጽዕኖ መደናቀፍ እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ጋዲሳ ተስፋዬ እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን አንድ የልማት ፕሮጀክት ስራ ብቻ ሳይሆን የህልውና መገለጫና ከደህንነት መውጫ ማሳያ መንገድ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን አስተሳሰብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው መሆኑን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር ጋዲሳ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግብጽን ወግነው የተናገሩት ንግግር የዓለም ዓቀፍ የሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን ያላገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይ በሀገራት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በዓለም ዓቀፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሠረት ሀገራቶቹ ችግሮቻቸውን መፍታት እንዳለባቸው የሚደነግግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የስነምግባርና ስነዜጋ መምህር መገርሳ ነገራ በበኩላቸው ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የተሻለ የእድገት ተስፋ ያላት ሀገር መሆኗን ማሳያ ምልክት አድርገው እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የሀይል አቅርቦት ፍላጎትን በማሳካት አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲፈጠሩ አጋዥ ይሆናል ማለታቸውን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በኢትዮጵያውያን አንጡራ ኃብት እየተገነባ ያለውን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ትራምፕ ግብጽ ግድቡን ልትመታው ትችላለች ብለው መናገራቸው ከአንድ የሀገር መሪ የማይጠበቅና የአሜሪካውያንን ህዝብ የማይወክል ነው ሲሉ ገልፀዋል።
የፕሬዚዳንቱ ንግግር በአንጻሩ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ግድቡን ለመጨረስ እያደረጉ ባሉት ርብርብ ላይ የበለጠ ብርታት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም ጠቁመዋል።

The post የዶናልድ ትራምፕ አስተያየት ከአንድ የሀገር መሪ የማይጠበቅና የዓለም ዓቀፍ ህግን ያላገናዘበ ነው- የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply