#የጀርባ አጥንት መጉበጥ/Scoliosis/የጀርባ አጥንት መጉበጥ በተለምዶ ህጻናት ላይ የሚከሰት የወገብ ችግር ነዉ፡፡ነገርግን ችግሩ ህጻናት ላይ ብቻ ሳይሆን ወጣቶች ላይ እንዲሁም በዕድሜ የ…

#የጀርባ አጥንት መጉበጥ/Scoliosis/

የጀርባ አጥንት መጉበጥ በተለምዶ ህጻናት ላይ የሚከሰት የወገብ ችግር ነዉ፡፡

ነገርግን ችግሩ ህጻናት ላይ ብቻ ሳይሆን ወጣቶች ላይ እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ላይም ይከሰታል፡፡

በጣም የተለመደዉ ግን በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኙ ዕድሜያቸዉ ከ11-17 የሆኑ ልጆች ላይ ነዉ፡፡

#ብዙዎችን የሚያጋጥመዉ ‹‹አዶለሰንት ይዶፓቲክ ስኮሊዮሲስ›› ነዉ፡፡
ይዶፓቲክ ማለት ‹‹መንስዔዉ የማይታወቅ›› ማለት ነዉ፡፡
ይህም ዕድሜያቸዉ ከ10 ዓመት በላይ የሆነ ታዳጊዎች ላይ የሚከሰት ነዉ፡፡
የነርቭ ዘንግ ችግር፣ የአከርካሪ አጥንት ችግር፣ የጡንቻ ችግር ሳይኖራቸዉ ችግሩ ሊያጋጥማቸዉ ይችላል፡፡

ለዚህ እንደ ምክንያትነት የሚነሱ የተለያዩ ዓይነት መላ ምቶች አሉ፤ የሆርሞን መዛባት፣ የንጥረ ነገሮች መዛባት፣ የጡንቻዎች መዛባት ይነሳሉ ነገርግን የተረጋገጡ አይደሉም፡፡

#መነሻ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?

የተለያየ የዕድሜ ክልል ዉስጥ የተለያዩ ምክንያቶች አሉት
የመጀመሪያዉ ከእርግዝና ወቅት ጀምሮ የሚኖር የጀርባ አከርካሪ አጥንቶች መዛባት ነዉ፡፡
ሌላኛዉ የአከርካሪ አጥንት ሙሉ ለሙሉ አለመፈጠር
በከፊል መፈጠር
ተያይዞ መፈጠር/ምክንያቱም እያንዳንዱ አከርካሪ አጥንቶች ክፍተት አላቸዉ፡፡/
የነርቭ ዘንግ አፈጣጠር ችግር እንደ ምክንያትነት ይነሳሉ፡፡

#ምልክቶቹስ ምንድናቸዉ?

የመጀመሪያዉ የትከሻ መዛነፍ ነዉ፡፡
የደረት አጥንቶች መዛነፍም ይኖራል፡፡
ጎብጦ መታየት
ዝቅ ብሎ ያለዉ ወገብ እኩል ያለመሆን
አንድ እግር ማጠር /ሲራመዱም ዘምበል ብሎ መሄድ/
ይህን በቅድሚያ ቤተሰብ የሚያስተዉለዉ ነዉ፡፡

#በህክምና ምርመራ ወቅት በሚነሳ ኤክስሬይ አማካይነት ደግሞ ሌሎች ምልክቶች ይታያሉ፡፡

የመጀመሪያዉ አጥንቱ የታጠፈበት ዲግሪ ሲለካ ከ10 ዲግሪ ጀምሮ ያለ ከሆነ የአጥንት መጉበጥን የሚያሳይ ነዉ፡፡
ከዛ በታች ከሆነ ግን የአጥንት መጉበጥ ትርጓሜን ስለማያሟላ ተከስቷል አልያም አጥንት መጉበጥ አለ ለማለት አይቻልም፡፡

#የመጉበጡ መጠን ሲለካ ታዲያ አብሮ የሚታዩ የተለያዩ ጉዳዮች አሉ፡፡
በልኬቱ ወቅት ትልቅ መጉበጥ ወይም እስከ 40 ድግሪ መጉበጥ ከተገኘ በጣም ቶሎ እየጨመረ የመሄድ ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
ከ20 ድግሪ በታች ያሉ መጉበጦች ግን እየጨመረ የመሄድ ዕድላቸዉ ዝቅተኛ በመሆኑ ብዙም የሚያሰጉ አይሆንም፡፡

#ትኩረት የሚሰጣቸዉ ጉዳዮች ምንድናቸዉ?

የመጀመሪያዉ የመጉበጥ መጠኑ
መጉበጥ የጀመረበት ዕድሜ
መጉበጥ ያለዉ ታካሚ ዕድገቱ በጣም የሚጨምርበት ዕድሜ ላይ ከሆነ ችግሩን ከፍ ያደርገዋል፡፡

ለምሳሌ አንዲት ሴት ልጅ የወር አበባ ማየት ከመጀመሯ በፊት ያለዉ አንድ አመት እና ካየች በኋላ ያሉት ሁለት ዓመታት በጣም ፈጣን ዕድገት የምታሳይበት በመሆኑ መጉበጡም በከፍተኛ ፍጥነት የሚያድግ ነዉ የሚሆነዉ፤ ወንዶችም አዶለሰንስ ላይ ሲሆኑ ከፍተኛ ዕድገት ስለሚያሳዩ በዚህ ጊዜ የሚከሰት መጉበጥ በፍጥነት ህክምና የሚያስፈልገዉ ነዉ፡፡
ታካሚዉ ዕድገቱን ከጨረሰ በኋላ የሚያጋጥሙ መጉበጦች ግን የመስፋፋት ዕድላቸዉ ያነሰ ስለሚሆን ብዙም አያሰጉም፡፡

#ለአጥንት መጉበጥ ቅድመ መከላከል ማድረግ ሊከብድ ይችላል፡፡

ችግሩ መኖሩን ቀድሞ ማወቅ ግን የተሻለ ነዉ፡፡

ጨቅላ ህጻናት ላይ ለሚፈጠረዉ ችግር በእርግዝና ወቅት በሚደረግ ክትትል አልያም ሲወለድ የሚታይ በመሆኑ ወደ ህክምና ቶሎ የመምጣት ዕድል አለ፡፡
ዕድሜያቸዉ ለትምህርት የደረሱ ልጆቻችንን ደግሞ ‹‹አዳምስ ፎርዋርድ ቤንድ ቴስት›› የሚባል የመጉበጥ መጠንን የሚለካ አሰራር ስላ ያንን በመጠቀም ማወቅ እንችላለን፡፡
ልጆችን ዕራቁታቸዉን አስጎንብሶ የዉሃ ልክ መለኪያ ጀርባቸዉ ላይ በማድረግ የልጆቻችንን የአጥንት መጉበጥ መለየት እንችላለን፡፡
ዉሃ ልክ መለኪያዉ ወደ 7 ዲግሪ የሚጠጋ መዛነፍ ካለ መጉበጥ ስላለዉ ወደ ህክምና መዉሰድ ይመከራል፡፡

#ህክምናዉ ምን ይመስላል?

ህክምናዉ እንደ ምክንያቶቹ የሚለያይ ነዉ፡፡
መጉበጡ እንደተገኘበት ዕድሜ ፣ እንደ ዕጥፋቱ መጠንም ይወሰናል፡፡
የአከርካሪ አፈጣጠር ችግር ያለባቸዉ ከሆኑ በተለይ ደግሞ በአንድ በኩል የዘጋ አልያም በአንዱ በኩል በከፊል መፈጠር ያላቸዉ ልጆች ካሉ ይህ ግዴታ የቀዶ ህክምና የሚያስፈልገዉ ነዉ፡፡

ወጣቶችም ሆኑ በእድገት ላይ ያሉ ልጆች ከ30-40 ድግሪ ያለ የመጉበጥ መጠን ያላቸዉ ከሆኑ ደግሞ በቀዶ ህክምና ቢታከሙ የተሻለ ነዉ፡፡
ከ20-30 ዲግሪ ያሉት ደግሞ ድጋፍ ብሬስ በሚባሉ የድጋፍ አይነቶች ከዉጪ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በጣም ህጻን ከሆኑ ደግሞ በጄሶ የሚታሰር ይሆናል፡፡
ከ20 ዲግሪ በታች ያሉ ከርቮች ደግሞ ክትትል ብቻ ነዉ የሚያስፈልጋቸዉ ሲሆን ሌላ ተጨማሪ ህክምናን አይፈልጉም፡፡

የአጥንት እና አደጋ ስፔሻሊስት እና የአከርካሪ ቀዶ ጥገና ሰብ-ስፔሻሊስት ከሆኑት ከዶ/ር ቃልአብ ተስፋዬ ጋር ስለ የጀርባ አጥንት መጉበጥ ከተደረገ ቃለ መጠይቅ የተወሰደ፡፡

በእስከዳር ግርማ

መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply