
የጅማ ደብረ መዊዕ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ከበባ ተደርጎበታል! የካቲት ፩ ቀን ፪፼፲፭ ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ የጅማ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና የሚገኝበትን ደብረ መዊዕ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን ሰብሮ ለመግባት ከፍተኛ የጸጥታ ኃይል የቤተ ክርስቲያኑን ቅጽር ከብቦ መቆሙና በዚህም ውጥረት መንገሡ ተገለጸ። የኦሮሚያ ፖሊስና ልዩ ኃይል ሀገረ ስብከቱን ለ22 ዓመታት ያህል ያስተዳድሩትን ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ከጅማ አየር ማረፊያ እንዲመለሱ ካደረገ በኋላ ሕገ ወጡን ቡድን ለማስገባት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የጅማ ምእመናንና ምእመናት ግን ይህንን ሕገ ወጥ ሹመት በመቃወም አድባራቶቻቸውን በመጠበቅ ላይ ናቸው። ነገር ግን የኦሮሚያ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የደብሩ በር ዘግቶ በመቆም ከውጪ ሌሎች ምእመናን እንዲጠጉ እንደማይፈቅዱና በሩቅ እየመለሷቸው እንደሚገኙም መረጃ አድራሾቻችን ጠቁመዋል። በዚህም ምክንያት ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ ምንም ዓይነት ምግብ እየገባላቸው እንዳልሆነና ለቀብር የሚመጡ ኦርቶዶክሳውያንን ሳይቀር ደብቀው ምግብ ያስገባሉ በሚል ጥርጣሬ ከፍተኛ ፍተሻ እንደሚደረግባቸውም ነው የተነገረው። በተጨማሪም ጥቁር ልብስ የለበሱ ምእመናንን ጨምሮ በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ካህናት አባቶችን ጭምር እያሠሩ እንደሚገኝ ተጠቅሷል። እስካሁን ድረስም አባ ተክለ ሃይማኖት የሚባሉ የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይን አሥረዋል። ከዚህም በተጨማሪም የደብረ መዊዕ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ለሆኑት መልአከ መዊዕ አባ አብርሃም ከቤተ ክርስቲያኑ ግቢ እንዲወጡ ከጸጥታ ኃይሉ ደብዳቤ እንደተላከባቸውም ነው የተገለጸው። ምእመኑ እንዲወጡ ለማግባባት እየሞከሩ ቢሆንም ብንወጣም ቤት ለቤት ተለቅመን እንታሠራለን እዚሁ ሆነን የሚመጣውን መከራ እንቀበላለን በሚል አቋም ጸንተው እየጠበቁ መሆናቸው ነው የተነገረው። ምንጭ፦ የተዋህዶ ሚዲያ ማዕከል “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post