You are currently viewing የጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ስራ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሊደረግ ነው

የጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ስራ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሊደረግ ነው

ዋዜማ- በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ታሪክ ከአምስት አስርት ዓመታት በኋላ የውጭ ባለሀብቶች በሀገር ውስጥ የጅምላ እና የችርቻሮ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ የሚፈቅድ የህግ ማእቀፍ ተጠናቆ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ስምታለች።

ለኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ ተከልሎ የነበረውን የጅምላ እና የችርቻሮ ንግድ ስራን ለውጭ ዜጎች የሚፈቅደው ህግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሚመራው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ፤ ለኢትዮጵያውያን ተከልሎ የቆየውን የወጪ እና ገቢ ንግድን እንዲሁም የጅምላ እና ችርቻሮ ንግድን ለውጭ ባለሀብቶች የሚፈቅድ መመሪያ ተዘጋጅቷል ።

ይህ የመንግስት እርምጃ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለውጪ ውድ ድር ክፍት የማድረግ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህም ሀገሪቱ አለማቀፍ አበዳሪዎች ድጋፍ እንዲደርጉላት የተወሰደ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል በጉዳዩ ላይ ያወያየናቸው ባለሙያዎች ነግረውናል። ተያያዥ ዘገባ በዚህ ማስፈንጠሪያ ዘልቀው መመልከት ይችላሉ

በመመሪያው ላይም የውጭ ዜጎች በሀገር ውስጥ በጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ላይ የሚሰማሩባቸው ሁኔታም ተቀምጧል ።

በዚህም መሰረት ከነዳጅ እና ማዳበርያ ውጭ የትኛውም የውጭ ዜጋ ፤ ባለሀብትም ሆነ ኩባንያ በጅምላ ንግድ ላይ መሰማራት እንደሚችል በመመሪያው ተቀምጧል ። የጅምላ ንግዱንም ከሀገር ውስጥ አምራች ገዝቶም ሆነ ከውጭ አስገብቶ ማከናወን እንደሚችልም ይጠቅሳል ። በሌሎች ህጎች ለጅምላ ንግድ አስፈላጊ የሆኑ ዝቅተኛ የካፒታል መጠን እና ተያያዥ ህጎች እንዳሉ ሆነው ፤ የውጭ ባለሀብቱ በጅምላ ንግድ ላይ መሰማራት ከፈለገ ዘመናዊ የሆነ የገበያ መሰረተ ልማት ለመገንባት ከመንግስት ጋር ውል መግባት አለበት ፤ ከዚህም ባለፈ የጅምላ ንግዱን የሚያቀላጥፍ የሎጂስቲክስ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበትም ተደንግጓል ።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርም ዘመናዊ የገበያ መሰረተ ልማት ሊያሟላቸው የሚገቡ ደረጃዎች በተመለከተ ህግ እንደሚያወጣም በመመሪያው ተጠቅሷል ።

በችርቻሮ ንግድ ላይ የውጭ ባለሀብቶች መሳተፍ እንደሚችሉም በመመሪያው የተቀመጠ ሲሆን ፤ በችርቻሮ ንግድ ላይ ለመሰማራት በሌላ ህግ ላይ የተደነገጉ ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ ሆነው ፤ በችርቻሮ ንግድ ላይ መሰማራት የሚቻልባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል ።

የመጀመርያው በችርቻሮ ንግድ ላይ መሰማራት የሚፈልግ የውጭ ባለሀብት ቢያንስ በ2000 ካሬ ሜትር የወለል ስፋት ቦታ ላይ የሚካሄድ እና በአንድ ባለቤት የሚመራ ቅርጽ ያለው የንግድ ስራ ሆኖ ፤ በሶስት አመታት ውስጥ አምስት ትልልቅ የገበያ ማእከላትን (ሱፐር ማርኬት)ለመገንባት ግዴታ ውስጥ የሚገባ መሆን እንዳለበት እና ፍቃድ ለማግኘትም ቢያንስም ሁለቱን የገበያ ማእከላት የመክፈት ሂደት ማጠናቀቅ እንዳለበት ተቀምጧል ።

በሌላ አማራጭ ደግሞ ቢያንስ በ5000 ካሬ ሜትር የወለል ስፋት ላይ በችርቻሮ ንግድ ላይ መሰማራት የሚፈልግ የውጭ ባለሀብት ፤ በአንድ ባለቤት የሚመራ ቅርጽ ያለው የንግድ ስራ ሆኖ ፤ በሶስት አመታት ውስጥ ሁለት ግዙፍና ከሱፐር ማርኬትም የሚበልጡ(ሀይፐር ማርኬት) ማቋቋም እንዳለበት እና ፍቃዱን ለማግኘትም ከዚህ ውስጥ የአንዱን ግዙፍ የገበያ ማእከል(ሀይፐር ማርኬት) የማቋቋም ስራን ማጠናቀቅ አለበት ሲል መመሪያው ይደነግጋል ።

በሶስተኛ አማራጭ ደግሞ ፤ የውጭ ባለሀብት በችርቻሮ ንግድ ላይ ለመሰማራት ቢያንስ 10 ሺክ ካሬ ሜትር የወለል ስፋት ባለው ቦታ እና በአንድ ባለቤት የሚመራ ቅርጽ ያለው ሆኖ ፤  ፍቃድ ለማግኘት ግን ሙሉ የንግድ ማእከል ግንባታውን ማጠናቀቅ እንደሚገባው ተደንግጓል ።

ሱፐር ማርኬት ፤ ሞል እንዲሆም ሀይፐር ማርኬት የሚባሉት ምደባዎች ማሟላት የሚገባቸው ደረጃዎች በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በንግድ ፍቃድ መመሪያ መሰረት የሚወሰን እንደሆነም ተነስቷል ።

ሆኖም አለም አቀፍ ስመ ጥር የሆነ የንግድ ስምን ይዘው በዚሁ ስያሜ ከላይ ከተጠቀሱት አማራጮች በአነስተኛ ቦታ እና ካፒታል ንግድ ላይ መሰማራት የሚፈልጉ የውጭ ኩባንያዎችን ጉዳይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ፍቃድ የሚያገኙበትን መንገድ በተለየ ሁኔታ ይመለከተዋል ሲል መመሪያው አካቷል ። 

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አዲስ ገጽታን የሚከስተው ይህ መመሪያ ተግባራዊ ሲሆን በተለይ የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ከፍተኛ የውድድር ተጋላጭነት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ስጋታቸውን የሚያነሱ አሉ ።

መንግስትም የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ተዘጋጁ ከማለት ውጭ ከውድድር ውጭ ሊሆኑ ቢችሉ ሊያደርግላቸው ስለሚችለው ድጋፍ ያስቀመጠው ነገር የለም ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ታማኝ ግብር ከፋይ ብሎ መንግስት ከሰየማቸው ነጋዴዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ጊዜ መንግስታቸው ይህንን መመሪያ እንዳዘጋጀ እና አለም አቀፍ እውቅና ያላቸው እነ ስታር ባክስን የመሳሰሉ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የመሰማራት እድል እንዳላቸው ፍንጭ ሰጥተው ነበር ። በወቅቱም ውይይቱ ላይ ለተገኙ ነጋዴዎች ” ተዘጋጁ ” ማለታቸው የሚታወስ ነው ።  [ዋዜማ]

The post የጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ስራ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሊደረግ ነው first appeared on Wazemaradio.

The post የጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ስራ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሊደረግ ነው appeared first on Wazemaradio.

Source: Link to the Post

Leave a Reply