
የገቢዎች ሚኒስትር 26 ሚሊየን ብር የሚገመት ምግብ እና አልባስ ለመተከል ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረገ፡፡ (አሻራ ታህሳስ 21፣ 2013ዓ.ም) የገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌው ድጋፉን በሰጡበት ወቅት አምራች የሆናችሁ ወገኖቻችን መፈናቀላችሁ እናንተም ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ያስርባል፡፡ ድጋፉ ለጊዜው እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አይደለም ያሉት አቶ ላቀ፣ የአመራር ስነዘዴያችን እንዲስተካከል እንስራለን ብለዋል፡፡ በሀገራችን ያለው መፈናቀል እና ጅምላ ግድያ መንስኤው እኛ ራሳችን አመራሮች ነን ያሉት አቶ ላቀ፣ አመራሩ በአንድ በኩል የአመራር ቸልተኝነት ሲከፋ ደግሞ በማፈናቀል እና ግድያ በመሳተፉ የመጣ ችግር እንደሆነ እረዳለሁም ብለዋል፡፡ ለዚህም አግላይ መንግስታዊ አሰራርን በማስተካከል፣እናንተም እንደ ህዝብ ለመብታችሁ በመደራጀት ልትቆሙ ይገባል ብለዋል፡፡ ወቅቱ ኢትዮጵያን በጋራ የምንድንበት ነው፣ለዚህ ደግሞ አግላይ አሰራሮችን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ገቢዎች ሚኒስትር እስካሁን በኮንትሮባንድ ከተያዘ ሸቀጣሸቀጥ ወደ ሶስት ቢሊየን ብር አካባቢ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግር ለደረሰባቸው ንፅሃን ድጋፍ ማዋሉንም ተነግሯል፡፡ በሌላ በኩል በተለያዮ ጊዜ ወደ ተፈናቃዮች የሚላክ እርዳታ በተገቢው መንገድ ለተፈናቀሉት እየደረሳቸው እንዳልሆነ ተፈናቃዮች ይናገራሉ፡፡ የመተከል አመራር በሚመቸው መንገድ ሲያከፋፍል ቆይቷል፡፡ ድባጤ አካባቢ የኦነግ ታጣቂ ቡድን የመንግሥት መዋቅሩን እንደገና እየተቆጣጠረው እና ንፅሃንን እየገደለ መሆኑም ተሰምቷል፡፡ የመተከል ጉዳይ እንዲረጋጋ ከመሰረቱ የአመራር እና የተቋም ግንባታው ፍትሃዊ መሆን አለበት እየተባለ ነው፡፡ እስካሁን የመተከል ተፈናቃዮች ቁጥር 120 ሺ አካባቢ የደረሰ ሲሆን፣በአንድ ወር ውስጥ ብቻ የተገደሉት ደግሞ 967 ደርሰዋል፡፡ አሁንም በአካባቢው የኦነግ ታጣቂ ሀይል አባይን ተሻግሮ መተከል እንደገባ ለአሻራ ጥቆማዎች እየመጡ ነው፡፡
Source: Link to the Post