የገዛ ሚስቱን በካራ አንገቷንና ጉንጯን በመውጋት እንዲሁም ምላሷን በመቁረጥ የገደለው ተከሳሽ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ

ሐሙስ ሰኔ 30 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በምዕራብ ጎጃም ዞን በሰሜን አቸፈር ወረዳ ለግድያ ቀበሌ አይጣ በተባለው መንደር ውስጥ የገዛ ሚስቱን በካራ አንገቷንና ጉንጯን በመውጋት እንዲሁም ምላሷን በመቁረጥ ከባድ የሰው መግደል ወንጀል የፈጸመው ተከሳሽ በ25 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ።

ተከሳሹ ብርሃኑ ቆየ ዓለሙ የተባለ የእድሜ 33 ግለሰብ ሲሆን፤ በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚተዳደር ነው። ተከሳሹ ሰው ለመግደል አስቀድሞ በማሰብ የግል ተበዳይ ወርቄ አደራ የተባለችውን መስከረም 26 ቀን 2014 ከንጋቱ 11 ስዓት አካባቢ ሲሆን፤ በካራ አንገቷን ኹለት ጊዜ በመውጋት ጉንጯን በመቅደድ እና ምላሷን በመቁረጥ አሰቃቂ በሆነ መንገድ የገደላት በመሆኑ ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ፈጽሟል በማለት ዐቃቢ ህግ ማስረጃዎችን ዘርዝሮ ክስ አቅርቧል፡፡

ተከሳሹ በችሎት ቀርቦ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም በማለት የቀረበበት ክስ ክዶ ተከራክሯል፡፡

የክሱን መካድ ተከትሎ፤ ዐቃቢ ህግ እንደክስ አቀራረቡ ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮቹን አስቀርቦ አሰምቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የዐቃቢ ህግን ማስረጃዎችን መርምሮ የገዛ ሚስቱን በካራ አንገቷንና ጉንጯን በመውጋት ምላሷን የቆረጣት መሆኑና ከተለያዩ የሰውነት ክፍሏ ላይ በስለት በመውጋት በአሰቃቂ ኹኔታ የገደላት መሆኑን፣ ሟችም መጫት የነበረች ስለመሆኗ በማስረጃ የተረጋገጠበት ስለሆነ እንዲከላከል ብይን ሰጥቶ የመከላከያ ምስክር የለኝም በማለት በራሱ ፈቃድ የመከላከል መብቱን የተወው በመሆኑ፤ የወንጀል ህግ አንቀጽ 539 ንኡስ አንቀጽ 1 ሀ ላይ የተመለከተውን ተላልፎ ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ፈጽሞ በመገኘቱ ጥፋተኛ ተብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱም የተከሳሹን ጥፋተኝነት ተከትሎ በዐቃቢ ህግና በተከሳሹ በኩል የቀረቡትን የቅጣት አስተያት ተቀብሎ ከተገቢው ህግ ጋር ከመረመረ በኋላ ተከሳሹን ያርማል፣ ያስተምራል፣ ሌላውንም ማህበረ-ሰብ ያስጠነቅቃል ብሎ ያመነበትን በ25/ሃያ አምስት /ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የባህርዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ውሳኔ ማስተላለፉን ከከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply