በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ብሔረሰብ ዞን ዲማ ወረዳ፣ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በተጨማሪ ከደቡብ ሱዳን ድንበር አቋርጠው በሚገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የሚፈጸመው ተዳጋግሚ ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የዲማ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የዲማ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ኡመድ ኦቶ፤ “ለደቡብ ሱዳን እና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አጎራባች የሆነው የዲማ ወረዳ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ሕገወጥ ታጣቂዎች በተጨማሪ፤ ከደቡብ ሱዳን ተነስተው ወደ ወረዳው የሚገቡ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ የሚያደረሱት ጥቃት ከወረዳው አቅም በላይ ሆኗል።” ብለዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም፤ ታጣቂዎቹ በወረዳው በሰላም የሚኖሩ ዜጎችን እንደሚገድሉ፣ መኖሪያ ቤቶችን እንደሚያቃጥሉ እና የቤት እንስሳትን እንደሚዘርፉ ነው የገለጹት፡፡
ታጣቂዎቹ ከዲማ ወረዳ በተጨማሪ በክልሉ በሚገኙ የአኝዋክ እና የኑዌር ብሔረሰብ ዞን ውስጥ ባሉ ወረዳዎች ላይ ጥቃት እያደረሱ መሆኑን በመጠቆም፤ ለአብነትም ባለፈው ዕሮብ ሐምሌ 12/2015 በአቦል ወረዳ በጠራራ ጸሐይ 12 ነዋሪዎችን መግደላቸውን ገልጸዋል፡
በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሠራዊት ወደ ወረዳው ገብቶ የአካባቢውን ሰላም እያስከበረ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ “ይሁን እንጂ ታጣቂዎቹ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በማይኖሩባቸው አካባቢዎች እየተዟዟሩ ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።” ነው ያሉት።
በክልሉ ባለፈው ዕሮብ ሐምሌ 12/2015 የአኝዋክና ኑዌር ጎሳዎች በሚገናኙባቸው የኢታንግ ልዩ ወረዳ ቀበሌዎችና በጋምቤላ ከተማ በተከሰተ ግጭት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸው ይታወሳል።
Source: Link to the Post