የግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብ በመሙላቱ ምክንያት ግድቡን ለማስተንፈስ የተለቀቀው ውሃ የጎርፍ አደጋ እንዲከሰት አድርጓል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብ በመሙላቱ ምክንያት ግድቡን ለማስተንፈስ የተለቀቀው ውሃ የኦሞ ወንዝ በከፍተኛ መጠን እንዲሞላ እና ወንዙ ከዚህ ቀደም በጎርፍ ከሚያጥለቀልቃቸው ቦታዎች በተጨማሪ በሌሎች ቦታዎች ላይ የጎርፍ አደጋ እንዲከሰት አስተዋጽዖ ማድረጉ ኮሚሸኑ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ውስጥ ባሉ 12 የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አግባብነት ካላቸው ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ሕጎችና ሰነዶች አንጻር መገምገሙን አስታወቀ፡፡

በግምገማውም የመፈናቀል መንስኤዎችን፣ በመፈናቀል እና ድኅረ መፈናቀል ወቅት የደረሱ ጉዳቶችን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እና አሳሳቢ ሁኔታዎችን መለየቱን ነው ያስታወቀው፡፡

የኦሞ ወንዝን በከፍተኛ ሁኔታ መሙላት እና የዳሰነች ወረዳ በርካታ አካባቢዎችን በጎርፍ መጥለቅለቅ ተከትሎ፣ ሰዎች ለመፈናቀል ከመዳረጋቸው ባሻገር በሕይወታቸውና በንብረታቸው እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን በሚያገኙባቸው ተቋሟት ላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑን የክትትል ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በዚህም መሠረት ልዩ ድጋፍ የሚሹ ተፈናቃዮችን ቅድሚያ በሰጠ መልኩ ለተፈናቃዮች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ ሰብአዊ ድጋፍ የማቅረቡ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ስምምነት (የካምፓላ ስምምነት) አባል ሀገር እንደመሆኗ መንግሥት በስምምነቱ የተጠበቁ መብቶችን በተቻለ መጠን እና ፍጥነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

እንደዚሁም በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት የሚከሰት መፈናቀልን ለማስወገድ እና መፈናቀል ሲከሰትም የሰብአዊ መብቶች መርሖችን የተከተለ ዘላቂ መፍትሔ ለማመቻቸት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል።

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ግንቦት 15 ቀብ 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply