የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከምርጥ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ተካተተ፡፡ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ “የሠላም ዩኒቨርሲቲ”…

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከምርጥ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ተካተተ፡፡ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ “የሠላም ዩኒቨርሲቲ” በመባል የሚታወቀው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከዓለም አቀፍ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ተካቷል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከዓለም አቀፍ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች መካተቱን በማስመልከት ከአብመድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶክተር) ዩኒቨርሲቲው መለኪያ መስፈርቶችን በማሟላት ከዓለም አቀፍ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል መካተቱን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል ከዓለም ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ የተሰለፈ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ሆኗል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ ከሚባሉ 1 ሺህ 500 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 826ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ በአፍሪካ ደግሞ 20ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ምርጥ ዩኒቨርሲቲ ሆኗል ነው የተባለው፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ምርጥ ተብሎ መካተት ለዩኒቨርሲቲው ታላቅ ነገር መሆኑን ነው ዶክተር አስራት አፀደወይን የተናገሩት፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከዓለም አቀፍ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ መካተት ለተጨማሪ ሥራዎች እንደሚገፋፋም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ለአጋር አካላትም መነሳሳትን እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ትኩረቱን ምርምር፣ የድህረ ምረቃ ትምሕርትና ሌሎች ችግር ፈቺ የሆኑ ሥራዎች ላይ እንደሚያደርግም ዶክተር አስራት ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች 330 ሚሊዮን ብር ማስገኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የተመራማሪዎች ሥራ ለበርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥራ እድል መፍጠሩንም አመላክተዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስቀድሞ በሚታወቅበት በጤና፣ በሳይንስ፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ዘርፍ በበለጠ ጥንካሬ ይሠራል ብለዋል፡፡ በስነ ሕንጻ ንድፍ (አርክቴክቸር) ትምህርት ዘርፍም ትኩረት እንደሚደረግ የተናሩት ዶክተር አስራት በአካባቢው የሚገኙ ታሪካዊ የሕንጻ ጥበቦችን እንደ መነሻ በመውሰድ ሰፊ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አርክቴክቸር መምህራንም በገበታ ለሀገር ፕሮግራም ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከ30 ዓመት በላይ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎችን ደረጃ በማውጣት የሚታወቀው (usnews & world report) በቅርቡ በ81 ሀገራት በጀመረው የትምህርት ተቋማት ጀረጃ አሰጣጥ መሠረት ነው የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ከምርጥ 1 ሺህ 500ዎቹ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ያካተተው፡፡ (usnews & world report) ደረጃውን ያወጣው 13 የተለያዩ መመዘኛ መስፈርቶች በመጠቀም መሆኑም ታውቋል፡፡ ከመመዘኛዎቹ ውስጥ በዓለምአቀፍና በቀጣና ደረጃ የተደረጉ የምርምርና ጥናት ሥራዎች እውቅና፣ ለህትመት የበቁ የምርምርና ጥናት ሥራዎች ደረጃ፣ ዓለምአቀፍ ትብብርና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ አብመድ እንደዘገበው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply