
የጎንደር ዩኒቨርስቲ የጅኦሎጅ የምርምር ቡድን በቋራ ወረዳ ምን ያህል የብረት ማዕድን እንዳለ ጥናት አካሄደ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ጥናቱ የአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ ከጎንደር ዩኒቨርስቲ የጅኦሎጅ የምርምር ቡድን ውል በመውስድ በተለያዩ ቦታዎች ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝ የቋራ ወረዳ ማዕድን ጽ/ቤት ገልጧል። የወረዳ ማዕድን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ ታረቀኝ እንደገለፁት የጎንደር ዩኒቨርስቲ የምርምር ቡድን መሪ ዶክተር ዳዊት፣ ዶክተር አስፋ የፕሮቶ ማግኒቶ ሜትር ባለሙያ እና ሌሎች የምርምር ቡድኖች በተገኙበት ጥናቱ የተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል። አቶ ፍቅሬ እንዳሉት ጥናቱ በወረዳው ያለውን የብረት የማዕድን መጠን የይዘት ደረጃ ከአንድ ኩንታል ድንጋይ ስንት ኪሎ ግራም ማዕድን እንደሚገኝና የብረት ማዕድኑ በምን ያህል ቦታ ላይ ስፋት እንደሚገኝ ጥናት ማድረግ የቻሉ መሆኑን ገልፀዋል። ማዕድን አሁን ላይ በሃገራችን በኢኮኖሚ ሃብቱ ትኩረት ከሚሰጥባቸው አንዱ ዘርፍ ነው። ይህ ዘርፍ ደግሞ በወረዳው አካባቢውን የምንቀይርበት፣ ለብዙ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር፣ ሰፊ የልማት ውጤት የሚያመጣና የኢንዱስትሪ መንድር ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም የወረዳው ማዕድን ጽ/ቤት ዘርፍን ለማሳደግና የሚገኙትን የማዕድን ግብዓቶች በውጤት ለመቀየር ትኩረት አድርጎ የሚሰራ መሆኑን አሳውቀዋል። ጥናቱ አሁን ላይ በብረት ማዕድን የተጀመረ ሲሆን በሌሎች የማዕድን ዘርፎችንም ጥናት እንደሚደረግም ጠቅሰዋል። መረጃው_የቋራ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ነው።
Source: Link to the Post