
የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ሕገ ወጡን የወሊሶውን “ሹመት” አወገዘ። የአማራ ሚዲያ ማእከል ጥር 15 2015ዓ/ም አዲስ አበባ የጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባኤ ዛሬ ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም በሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰብሳቢነት ባካሔደው አስቸኳይ ጉባኤ ሃይማኖታዊ ክህደት ፣ ቀኖናዊ ጥሰት እና አስተዳደራዊ ግድፈት የታየበትን የወሊሶውን “ሹመት” አወገዘ ቅዱስ ሲኖዶስ ተገቢውን ውሳኔ እስኪሰጥ ምዕመናን በጸሎት እንዲቆዩ አሳሰበ። ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጸመው ሁሉን አቀፍ ክህደት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ያደረገ ሲሆን ክህደቱን የፈጸሙት አካላት ሥልጣን የሰጣቸውን መዋቅር (ተቋም) በመካድ የፈጸሙት ድርጊት እጅጉን አሳዛኝ ነው ብሏል። የተፈጸመው ጉዳይም ሕገ ወጥና ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ወንጀል ነው ያለው አስተዳደር ጉባኤው በምንም መመዘኛ ይህን ከፈጸሙ አካላት ጋር መደራደር በተዘዋዋሪ የቤተ ክርቲያናችንን ሕግና ሥርዓትን ማፍረስ ነው ብሏል። በማያያዝም ጎሰኝነት ኑፋቄ መሆኑን የገለጸው አስተዳደር ጉባኤው ይህን በመሰለ ተመሳሳይ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት የተጸሙ ክህደቶች በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ተነቅፏል ካለ በኃላ በቋንቋ መማና ማስተማር ችግር እንዳልሆነ በመረዳት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ አባቶችን በመሾም አገልግሎት እንዲሰጡ ስታደርግ መቆየቷን ሕገ ወጥ ድርጊቱን ከፈጸሙ አካላት በላይ ማስረጃ አይኖርም ብሏል። ጉባኤው ለቅዱስ ሲኖዶስ የውሳኔ አካል ሊሆኑ የሚችሉ የውሳኔ ሀሳቦችን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ከሕግ አንጻር በመነሳት የጠቆመ ሲሆን የተፈጸመው ክህደት ከቀኖና ቤተክርስቲያንና ከሕግ አንጻር አንዴት እንደሚገለጽ የሚያመለክት ሰፊ የሚዲያ ሥራ እንዲሰራ በመወሰንና በቂ ማብራሪያ የሚሰጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በመመደብ ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም ቋንቋዎች ማብራሪያ እንዲሰጥ ወስኗል። ሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ተቋማቱን በንቃት መጠበቅና ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚተላለፍ መመሪያን በትጋት መጠበቅ እንደሚገባና አስፈላጊው መመሪያ በአስቸኳይ እንዲተላለፍ የወሰነው አስተዳደር ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን ላይ ክህደት የፈጸሙ አካላት ወይም የሿሚና ተሿሚ ነን ባዮች ደመወዝ እንዲታገድ፣ በተቋማችን ውስጥ የሚገለገሉባቸው ቢሮዎችና ማረፊያ ቤቶች በአግባቡ እንዱቀጠቁ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን መንግስትም እያደረገ ያለውን የቤተ ክርስቲያናን ጥበቃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ጠይቋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ምዕመናንና ምዕመናት ከጸሎት በተጨማሪ መዋቅራዊ መመሪያዎችን በትዕግስት እንዲጠብቁ አደራ በማለት የዕለቱን ስብሰባ በጸሎት አጠናቋል። ዘገባው የኢኦተቤክ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ነው። ምንጭ ተሚማ
Source: Link to the Post