የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የ2013 ዓ.ም. በጀት: ከ559 ሚሊዮን ብር በላይ ኾኖ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸደቀ፤ የምልአተ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ቀትር ላይ ይጠናቀቃል፤ 9:00 መግለጫ ይሰጣል

https://1.gravatar.com/avatar/7f09202441ad3b4b636e88820d6a7061?s=96&d=identicon&r=G
  • ለአብነት ትምህርት ቤቶች ማጠናከሪያ፡- 38,745,513.00
  • ለአህጉረ ስብከት ካህናት ማሠልጠኛዎች፡- 12,598,179.00
  • ለገጠር አብያተ ክርስቲያንና ለጥንታውያን ገዳማት መደጎሚያ፡- 7,747,970.00
  • ለቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ እና ለሦስቱ መንፈሳውያን ኮሌጆች፡- 41,750,926.61

***

የቤተ ክርስቲያንን ዓመታዊ በጀት የማጽደቅ፣ ተግባራዊነቱንም የመቆጣጠር ተግባር እና ሓላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከ559ሚሊዮን 857ሺሕ 509 ከ91 ሳንቲም፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የ2013 ዓ.ም. በጀት አጸደቀ፡፡ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በመጨረሻም፣

ባለፈው ዓመት በሥራ ላይ ከዋለው 688 ሚሊዮን 650ሺሕ 066 ከ44 ሳንቲም ጠቅላላ በጀት ሲነጻጸር፣ የዘንድሮው በጀት፣ ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ልዩነት አንሶ ታይቷል፡፡ ለበጀቱ መደበኛ የገቢ ምንጭ የኾነው አህጉረ ስብከት ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚልኩት የ35 በመቶ ፈሰስ፣ በ2012 ዓ.ም. ከነበረው 333 ሚሊዮን 699ሺሕ 606 ከ69 ሳንቲም ይልቅ፣ ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. በኋላ የተመዘገበው፣ 339 ሚሊዮን 725ሺሕ 272 ከ68 ሳንቲም የተወሰነ ብልጫ ማስመዝገቡ ታውቋል፡፡

ለዘንድሮው ከጸደቀው ጠቅላላ በጀት ውስጥ፣ 145ሚሊዮን 268ሺሕ 917 ከ44 ሳንቲም፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ለብፁዓን አባቶች ደመወዝ፣ ለቋሚ ዕቃ ግዢ እና ሥራ ማስኬጃ እንዲሁም ለአህጉረ ስብከት ደመወዝ እና ሥራ ማስኬጃ ወጪ የተመደበ ነው፡፡ በመሠራት ላይ ላሉ ውል ለተገባላቸው ሕንፃዎች ክፍያ የተያዘው ብር 85 ሚሊዮን፤ ለብፁዓን አባቶች፣ ለመንፈሳዊ ኮሌጆች እና ድርጅቶች ተሽከርካሪዎች ግዢ የተያዘው ብር 60 ሚሊዮን የበጀቱ ከፍ ያሉ ወጪዎች ናቸው፡፡

ለአራቱ መንፈሳውያን ኮሌጆች(ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ፣ ለሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ለአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ) በድምሩ፣ ብር 41 ሚሊዮን 750ሺሕ 926 ከ61 ሳንቲም በጀት ተመድቧል፡፡ በአህጉረ ስብከት ሥር ላሉ የካህናት ማሠልጠኛዎች ብር 12 ሚሊዮን 598ሺሕ 179፣ ለተዘጉ አብያተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት እና ለአብነት ት/ቤቶች ማጠናከሪያ ብር 39 ሚሊዮን 919ሺሕ 713፣ ለጥንታውያን ገዳማት መደጎሚያ ብር 6 ሚሊዮን 573ሺሕ 770፣ ለ18 የንባብ እና ቅዳሴ ት/ቤቶች 370ሺሕ ብር፣ ለአንድነት ገዳማት መንፈሳዊ ት/ቤት ማስፋፊያ ብር 853ሺሕ 066፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅት ብር 12 ሚሊዮን መመደቡ ተጠቅሷል፡፡

ከአህጉረ ስብከት የ35 በመቶ ፈሰስ በተጨማሪ፣ የመንበረ ፓትርያርኩ የመደበኛ ገቢ ምንጮች፥ የቤቶች እና ሕንፃዎች ኪራይ፣ የቁልቢ ርእሰ አድባራት ቅዱስ ገብርኤል ስእለት እና መባ፣ የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ የጎፋ ጥበበ እድ ካህናት ማሠልጠኛ እንዲሁም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ድጋፍ ገቢዎች ናቸው፡፡ የቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር እና ልማት ድርጅት የኪራይ ክፍያ ከሚሰበስብባቸው 1ሺሕ193 መኖሪያ ቤቶች፣ ድርጅቶች እና መጋዘኖች፣ ከ60 ሚሊዮን 980ሺሕ 170 ገቢ ማስገኘቱ ተጠቃሽ ነው፡፡

በሌላ በኩል፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ባለፈው ዓመት ከሀንጋሪ መንግሥት በተደረገላቸው ጥሪ ከኅዳር 12 እስከ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. በቡዳፔስት ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ በክርስትናቸው በደረሰባቸው ጥቃት የሕይወትና የንብረት ጉዳት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን መልሶ ማቋቋሚያ የለገሰው አንድ ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ፣ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ምልአተ ጉባኤው አሳስቧል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ቀጥተኛ ጥቃቱና የጥቃቱ ጫና እየደረሰባቸው ያሉ አህጉረ ስብከት በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተለይተው ገንዘቡ የሚከፋፈል ሲኾን፣ በአግባቡ ለተጎጂዎች አድርሰው ሪፖርቱን ከደጋፊ ሰነዶች ጋራ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንዲያስታውቁ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥብቅ መምሪያ ሰጥቷል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ባለፈው ጥቅምት 11 በመክፈቻ ጸሎት የጀመረውን የዓመቱ የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባውን፣ ዛሬ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚያጠናቅቅና ከቀትር በኋላ በ9፡00 መግለጫ እንደሚሰጥ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መመሪያ በፌስቡክ ገጹ ለብዙኃን መገናኛዎች አስታውቋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply