
የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ ሀይማኖታዊ ስርዓቱን፣ የአካባቢውን ወግ እና ባህልን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከብሯል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 11 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ ሀይማኖታዊ ስርዓቱን፣ ወግ እና ባህሉን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከብሯል። የጥምቀት በዓል አከባባበር በጎንደር ምን እንደሚመስል በስፍራው ተገኝቶ የተመለከተው አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) በዓሉ ሀይማኖታዊ ስርዓቱን፣ የአካባቢውን ወግ እና ባህልን ባከበረ መልኩ መከናወኑን ተመልክቷል። ጥር 10/2015 በድምቀት የተከበረው የከተራ በዓል ዛሬም በጥምቀት በዓል በላቀ ድምቀት አሸብርቆ እና ደምቆ መከበሩን ለማስተዋል ተችሏል። በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ የጎንደር እና የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከአማራ ብሎም ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲሁም ከውጭ በዓሉን ለማክበር የመጡ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ሀገራት ዜጎች ሀይማኖታዊ ስርዓቱን፣ የአካባቢውን ግ እና ባህል ገላጭ የሆኑ በልዩ ልዩ አለባበሶች አምረው እና ተውበው በመገኘት አክብረዋል። አረንጓዴ፣ቢጫ፣ቀይ ሰንደቅ አላማችን ከፍ ተብሎ በመሰቀል እየተውለበለበ ነው፤ በሰንደቁ ቀለም የተዋቡ ልዩ ልዩ ጌጣጌጦች፣ ባህላዊ አልባሳት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ለሸማቾች ቀርበው በስፋት እየተሸጡ መሆኑን ተመልክተናል። ከጥር 10/2015 ጀምሮ በርካታ ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባህሩ ገብተው አድረዋል። ይህን ተከትሎም ጥር 11/2015 ከንጋት ጀምሮ ወደ ባህረ ጥምቀቱ ያቀኑት የሀይማኖት አባቶች፣ በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ወገኖችና በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች በተገኙበት ጸሎት ከተደረገ እና መልዕክቶች ከተላለፉ በኋላ የመጠመቅ/የርጭት ስነ ስርዓቱ ተከናውኗል። ከህዝቡ ብዛት የተነሳ በመጠመቅ ወቅት መጨናነቅ እና መገፋፋት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። የጥምቀቱ ስነ ስርዓት በሰላም መጠናቀቁን ተከትሎ በከፍተኛ ዝማሬ፣ ወረብ፣ ባህላዊ ጭፈራ እና ጭብጨባ ታጅበው ታቦታቱ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። መንበረ መንግስት መድኃኒያለም፣ ደብረ ህሩዊያን አባ ጃሌ ተክለ ሀይማኖት እና የእልፍኝ ጊዮርጊስ እንዲሁም ቃሃ እየሱስ እና መጥምቁ ዮሃንስ ታቦታት ከጥምቀተ ባህሩ ወጥተው ወደ መንበራቸው ሲመለሱ ከጥምቀተ ባህሩ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ በምዕመናን ከፍተኛ እጀባ እና ክብከባ ተደርጎላቸዋል። በጥምቀተ ባህሩ የሚያድሩት ፊት ሚካኤል እና አጣጣሚ ሚካኤል በነገው እለት ወደ መንበራቸው የሚመለሱ ይሆናል። አበራ ጊዮርጊስ ስባረ አጽም ጥር የፊታችን ጥር 18፣ ሎዛ እና ቤዛዊት ማርያም ጥር 21 በአቅራቢያቸው እንዲወጡ ተደርጎ በዓሉ ከተከበረ በኋላ ወደ መንበራቸው የሚመለሱ ይሆናል። በተመሳሳይ ጭርቆስ፣ ሩፋኤል እና ተክለ ሀይማኖት በንግሳቸው በአካባቢያቸው እንዲወጡ ብሎም በዓሉ እንዲከበር ከተደረገ በኋላ ተመልሰው ወደ መንበራቸው እንደሚመለሱ አሚማ ያነጋገራቸው አባቶች ተናግረዋል። የጎንደር እና የአካባቢው ማህበረሰብም በብዛት ከምንጊዜውም የተለየ እንግዳን በአግባቡ ተቀብሎ በማስተናገድ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከብዙ ወገኖች ከፍተኛ ምስጋና ቀርቦለታል። የአልጋ እጥረት እንዳያጋጥም በሚል ቀድመው የተዘጋጁ ድንኳኖች፣ አድራሻቸውን በከተማ አስተዳደሩ በኩል ያስተዋወቁ የበጎ ፈቃደኞች ቤት ጭምር ጥቅም ላይ መዋላቸው ታውቋል። የጥምቀት በዓል ከጎንደር በተጨማሪም ባህር ዳርን፣ ደብረ ማርቆስን፣ ደብረ ብርሃንን፣ ምንጃር፣ ደብረ ታቦርን፣ እንጅባራን፣ ዳንግላን፣ ደሴን፣ ወልድያንና ኮምቦልቻን ጨምሮ በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች፣ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ፣ ብሎም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በድምቀት ተከብሯል። በጉራጌ ወልቂጤ ላይ ከገብርኤል ቤተክርስቲያን በነበረው ታቦት የማውጣት ስነ ስርዓት ሰረገላ ይገፉ ከነበሩ ወጣቶች መካከል ክብደቱ እና የሰረገላው ብረት ረጅም በመሆኑ ለመቆጣጠር አዳጋች እንደነበር ተገልጧል። ይህን ተከትሎም ከፖል ወደ ፖል ከተዘረጋው መብራት ሽቦ ጋር ብረቱ በመገናኘቱ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን እና በሁለት ወጣቶች ላይም ጉዳት መድረሱን የጉራጌ ዞን ፖሊስ ነው ያስታወቀው።
Source: Link to the Post