የጥምቀት ድባብ በኬኒያ እና ደቡብ ሱዳን በሚዋሰነው የአሪ ዞን

ጥምቀት በጽርዕ ቋንቋ “ኤጲፋኒ”፤ በግእዝ “አስተርእዮ”፤ በአማርኛው ደግሞ “መገለጥ” የሚል ትርጉም የያዘ  ቃል ነው። ቤተ ክርስትያን ከበዓለ ልደቱ  ቀጥላ ከቅጽረ  ቤተ ክርስትያን ወጥታ በዱር፣ በሜዳ፣ በወንዝና በባሕር ዳርቻ ጥር በየዓመቱ ጥር 11 በታላቅ ድምቀት የምታከብረው በዓለ ጥምቀት ነው።

ጥምቀት የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲተረጉሙ “ጥምቀት” በቁሙ፡- “ማጥመቅ፣ መጠመቅ፣ አጠማመቅ፣ ጠመቃ፣ የማጥመቅና የመጠመቅ ሥራ፣ ኅፅበት፣ በጥሩ ውኃ የሚፈጸም” በማለት ተርጉመውታል።

ቤተ ክርስትያን ከምታከብራቸው ዘጠኝ ዓበይት በዓላት አንዱ የሆነው በዓለ ጥምቀት ሲሆን መጋቢት 29 በዓለ ጽንሰት፣ ታህሳስ 29 የልደት በዓል እንዲሁም ጥር 11 ደግሞ የጥምቀት በዓሉ እንደሚከበር ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶቹ ያሳያሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የጥምቀት ክብረ በዓልን በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት መመዝገቡን ይፋ ያደረገው ታኅሣሥ 1 ቀን 2012 ነበር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንም የጥምቀት በዓልን በየዓመቱ በማኅሌትና በቅዳሴ በተለየ ሁኔታ ታከብረዋለች። በዋዜማው ታቦታቱ ከየአብያተ ክርስትያናቱ ወጥተው በወንዝ ዳር፣ በሰው ሰራሽ የውሃ ግድብም እንዲሁም በዳስ (ድንኳን) ያድራሉ።

ሌሊት ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ሥርዓተ ቅዳሴው የሚፈጸም ሲሆን ሲነጋ በወንዙ ዳር ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ አራቱም ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ በመርጨት ስርዓተ ጥምቀቱ ይጀመራል።

በቀድሞዉ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዘቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን፤ በአዲሱ አደረጃጀተ ደግሞ በአሪ ዞን ጂንካ ከተማ በዓሉ ያለዉን ልዩ ድባብ አዲስ ማለዳ አጠናቅራለች።

በዞኑ ጂንካ ከተማ በሚገኘው የደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርዔል ቤተ ክርስትያን አስተዳዳሪ መልአከ ጸሐይ መርጌታ ሰሎሞን ይመር ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ የጥምቀት በዓል ዓለም አቀፋዊ፣ ብሔራዊና ሃይማኖታዊ በዓል መሆኑን ይገልጻሉ።

በእስራኤላውያን እምነት በክርስትና እምነት እንደጥምቀት ይቆጠር የነበረው “ግዝረት” መሆኑን የሚያነሱት መርጌታ ሰሎሞን ይመር፤ በአዲስ ኪዳን ግን ከእየሱስ ክርስቶስ የዮርዳኖስ ጥምቀት በኃላ ጥምቀት የክስርስትና እምነት መቀበያ መሆኑን አንስተዋል።

ጥምቀቱ በዮርዳኖስ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱም “አዳምና ሔዋን ህግ ተላልፈው ከገነት ሲወጡ ዲያብሎስ የጨለማ ግርዶሽ ጋርዶ ፍዳ አጽንቶባቸው አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፤ አዳም የዲያብሎስ ወንድ አገልጋይ ነው፤ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ፤ ሔዋን ደግሞ የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ ናት። ብላችሁ ስመ ግብርናችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ” ማለቱን ያወሳሉ።

አክለውም “እነርሱም ፍዳ የሚያቀልላቸው መስሏቸው እንዳላቸው አድርገው አዘጋጅተው ሰጡት ዲያብሎስም ያንን የዕዳ ደብዳቤ አንዱን በሲዖል አንዱን በዮርዳኖስ ወንዝ አኖረው። ዲያብሎስ በዮርዳኖስ ወንዝ ያስቀመጠውን የዕዳ ደብዳቤ እየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ አጥፍቶታል” ብለዋል።

የዮርዳኖስ ወንዝ ዮር  እና ዳኖስ በሚል የሚከፈል ሲሆን ዮር በእስራኤል በኩል ያለው   ሲሆን ዳኖስ በአሕዛብ በኩል ያለው ነው። ሁለቱ አንድ ቦታ ላይ በሚገናኙበት ቦታ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቁን ይገልጻሉ።

የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና ዛሬ ምዕመኑ የሚጠመቀው ጥምቀት በውኃ ውስጥ በመዘፈቅ፣ ብቅ ጥልቅ በማለት ቢመሳሰሉም በትርጉማቸው ግን የተለያዩ መሆናቸውን ግን በአጽንኦት ይገልጻሉ። 

“ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው ትኅትናን ለማስተማር ነው፤ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወደ አገልጋዩ ቅዱስ ዮሐንስ መምጣቱ ራሱን ዝቅ አድርጎ መቅረቡንና ትኅትናን ለማስተማር መሆኑን መገንዘብ ይገባልም” ነው የሚሉት።

“ቅዱስ ዮሐንስ ‘አንተ በእኔ ልትጠመቅ አይገባም፤ እኔ ነኝ ባንተ መጠመቅ የሚገባኝ’ ባለው ጊዜም÷ ‘ፍቀድልኝ ትንቢቶች መፈጸምና ምሳሌዎቹም መከናወን አለባቸው’ በማለት ምላሽ ሰጥቶታል፤ እሱ መፍቀድ የሚገባው አምላክ ፈቃድን ከአገልጋዩ መጠየቁ ትኅትናን ለማስተማር መሆኑን መረዳት ይገባል” በማለት ያስረዳሉ።

እሳቸው በሚገኙበት የአሪ ዞን ጂንካ ከተማ ከእምነቱ ተከታዮች በተጨማሪ የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች እንዲሁም ቱሪስቶችም የክብረ በዓሉ ታዳሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

በዓሉ ሁልጊዜም አዲስ ነው የሚሉት መርጌታ ሰሎሞን፤ “እንኳን ቱሪስቶቹ እኛ የበዓሉ ባለቤቶች ራሱ ሁሌም እንደ አዲስ ነው የምናየው” በማለት ህዝቡ ከዓመት ዓመት በተለየ ድምቀት የሚያከብረው መሆኑን አንስተዋል።

ሆኖም ግን ይላሉ የጥምቀት በዓል ህዝባዊ በዓል እንደመሆኑ ከምንም በላይ በአገሪቷ ሰላም እና መረጋጋት ሊኖር እንደሚገባ አጽንዖት ይሰጣሉ።

አክለውም “መጀመሪያ ትልቁ ነገር ለአንድ አገልግሎት ሰላም ይቀድማል አይደል? ሰላም ከሌለ አገልግሎት የለም። በዓሉ የካህናቱ፣ የዲያቆናቱ እና የገልጋዩ በዓል አይደለም። የህዝብ በዓል ነው። ህዝቡ ይኼንን በዓል ወጥቶ የሚያከብረው ደግሞ ሰላም ሲሆን ነው” ይላሉ።

እንዲሁም ህብረተሰቡ ያለበት በርካታ ችግሮች በዓሉን በሙሉ ድምቀት ለማክበር እንዳይችል የራሱን አስተዋጾ እንደሚያደርግም ይገልጻሉ።

በመጨረሻም ለመላው ህዝበ ክርስቲያኑ እንኳን አደረሳቹ ያሉት የእምነት አባቱ፤ በዓሉን ከምንጊዜውም በተሻለ መተሳሰብ መከባበር እንዲሁም ወደ ቀደመ አንድነታችን የሚመለስበት ይሁን ሲሉም ምኞታቸውን ተናግረዋል።

የአሪ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ ታምራት ተስፋዬ በበኩላቸው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲውል የዞኑን ጸጥታ ኃይሎች እና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን የማስተባበር ስራ ተሰርቷል ብለዋል። 

ኃላፊው አክለውም አስፈላጊ የሆነው ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ዘንድሮ ለየት የሚያደርገው በመንግስት መዋቅር በአዲስ ዞን በመደራጀት ላይ ባለበት ሁኔታ የበዓል ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።

እንዲሁም በዞኑ የሚከበረው ጥምቀተ በዓሉ ቱሪዝምን ለመሳብ እንዲችል በርካታ ስራዎች መሰራታቸውንና እንግዶችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ወጣቶችም በበኩላቸው ለበዓሉ ድምቀት ከተማው ከማጽዳት ጀምሮ ባንዲራ መስቀል፣ የታቦት ማደሪያዎችን የማሰናዳቱን ስራ ቀድመው መጀምራቸውን ይገልጻሉ።

“ጂንካ ከተማዋ እንደዚ ደምቃ አታውቅም” የሚለው ደግሞ በጂንካ ከተማ ነዋሪ የሆነው ዲያቆን ሴኮ “ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ከተማዋ አሸብርቃለች” ሲል ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የዘንድሮው የጥምቀት በዓሉ አስተባባሪ የባዕታ ለማሪያም ቤተክርስቲያን መሆኑን የሚያነሳው ይሄው ወጣት በቅዳሴ፣ በአገልግሎቱ፣ በቅኔ ማህሌቱን እና ሌሎችም ስራዎችን የማስተባበሩ ኃላፊነት የደብሩ መሆኑን አንስቷል።

ነገር ግን ይላል ወጣቱ ዞኑ ከሌሎች አካባቢዎች ካለው ርቀት አንጻር ተገቢውን ትኩረት ማጣቱን ሳይገልጽ አላለፈም።

በተመሳሳይም በዲያቆን ሴኮ ሀሳብ የሚስማሙት የአሪ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ኤልያስ ሻቆ በዞኑ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው የዞኑ ከተማ አስተዳደር ጂንካ ከተማ ላይ ከቀድሞው የተለየ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

በዞኑ ባለው የቱሪስት መስሕብ እና ለጥምቀት ሶስት ሺህ የሚሆኑ የውጭ ቱሪስቶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በአዲሱ አደረጃጀት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስር የሚገኘው አሪ ዞን በደቡብ አቅጣጫ ከኬንያ፣ በደቡብ ምዕራብ ከደቡብ ሱዳን፣ በምዕራብ ከቤንች ማጂ፣ በሰሜን ከኮንታ፣ ጋሞ ጎፋና ባስኬቶ እንዲሁም ከኮንሶ ጋር ይዋሰናል።

የዞኑ የቀድሞ መጠሪያ ከኦሞ ወንዝ የተገኘ ሲሆን ኦሞ መነሻውን ከኦሮሚያ ክልል ሸዋ ተራሮች አድርጎ እስከ ደቡብ ኦሞ ዞን የ760 ኪሜ ጉዞ በማድረግ ወደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ተጉዞ ቱርካና ሀይቅን ይቀላቀላል።

በዞኑ 16 የሚሆኑ ብሔረሰቦች ያሉ ሲሆን ሙርሲ፣ አሪ፣ ኤርቦሬ፣ ኪይጉ፣ በና፣ ጸማይ፣ ሐመር፣ ዳሰነች፣ ካንጋቲ፣ ሙርሌ፣ ቦዲ፣ ካራ፣ ማሌ፣ ዲሜ፣ ብራይሌ እንዲሁም ባጫ ትርይብስ የሚሰኙ መጠሪያዎች አሏቸው።

ከዚህም ውስጥ በበርካቶች በተደጋጋሚ ሲባል ስለ ሚሰሙት ‘ሙርሲዎች’ ጥቂት እንበል በቁጥራቸው ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ስታትስቲክ ባለስልጣን መረጃ 7 ሺህ 500 መሆናቸውን ሲገልጽ በአንጻሩ አጥኚዎች 10 ሺህ ገደማ ናቸው ብለው ይገምታሉ።

አብዛኛው ማህበረሰብ ሙርሲዎች የሚያውቃቸው ከንፈር ተልትሎ በማስጌጥ ልማዳቸው እንዲሁም በዶንጋ ግጥሚያቸው ነው። ሴቶቻቸው ከንፈር እና ጆሮ ተልትሎ ሸክላ በማስገባት የማጌጥ ምርጫን የመፈፀም ወይንም ያለመፈፀም ፈቃድ አላቸው።

ሙርሲዎች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ‘ዶንጋ’ በእጃቸው መያዝ ያዘወትራሉ። ‘ዶንጋ’ በአማርኛ በትር ማለት ነው።

ይሄው በትርም ሙሴ ቀይ ባህር ከፍሎ እስራኤላውያንን እንዳሻገራቸው እነርሱም ‘ካዉሎ ኾሮ’ ሲሉ የሚጠሩት ጀግናቸው የኦሞን ወንዝ እንዲያቋርጡ እንደረዳቸው የሚነገር አፈታሪክ አለ።

በአጠቃላይ በዞኑ የማጎ ብሔራዊ ፓርክ ጥብቅ የአደን ክልሎች፣ ከፊል የኦሞ ፓርክ፣ ጨው ባህር በመባል የሚታወቀውን የዱር አራዊቶችና ወፎች መሰብሰቢያ፤ ታዋቂዎቹን ሰሚዝ (2 ሺህ 560 ሜ) እና የማጎ (2 ሺህ 538 ሜ) ተራሮችን ጨምሮ የብሔረሰቦች ባህላዊ የዕለት ተዕለት ክዋኔዎችና ባህላዊ በዓላት የቱሪስት መስህብ ናቸው።

በሐመር የከብት ዝላይ ‘ዶንጋ’፣ የሙርሲ መከታ ጨዋታ፣ ኬ-ኤል በቦዲ የዘመን መለወጫ በዓል ላይ የሚደረግ የወንዶች የውፍረት ውድድርና ጭፈራ ‘ዲሚ’ በዳሰነች የመጀመሪያ ሴት ልጅ የማስመረቅ ድግስ ‘ጂያር’፣ በአርቦሬ የሚከበር የገዳ በዓል እና በኛንጋቶም ወጣቶች ለአገር ቃል የሚገቡበት ሥርዓት የቱሪስት መስህብ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች ናቸው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply