የጨቅላ ህፃናት ሆድ ቁርጠት (Infantile colic)

የጨቅላ ህፃናት ሆድ ቁርጠት ችግር እናቶች በልጆቻቸው ህይወት የመጀመሪያዎቹ ወራት ውስጥ በጣም ከሚያሳስቧቸው ነገሮች አንዱ ነው፡፡
የህፃናት የሆድ ቁርጠት ብዙ ጊዜ ብዙ ህፃናት ላይ የሚከሰት ጊዜያዊ ችግር መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የህፃናት የሆድ ቁርጠት በተለይም እስከ 4 ወር ዕድሜ ያሉ ህፃናት ላይ የሚታይ ህመም መሆኑ ይነሳል።

በአለም አቀፍ ደረጃ አዲስ ከሚወለዱ ጨቅላ ህጻናት 20 ፐርሰንት የሚጠጉት የሆድ ቁርጠት ህመም ሊያጠቃቸው እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
እንዲሁም አዲስ ከሚወለዱ 4 ህፃናት አንዱ ይህ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ይነገራል፡፡
የጨቅላ ህፃናት ሆድ ቁርጠት ሲከሰት ልጁ የሆነ በሽታ አለበት ማለት እንዳልሆነ እና ከግዜ በኋላ ሊጠፋ የሚችል ነገር መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
በዚህ ጉዳይም ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን የህፃናት እና የጨቅላ ህፃናት ሀኪም ከሆኑት ዶ/ር ገስጥ መታፈሪያ ጋር ጣቢያችን ቆይታ አድርጓል፡፡

የህፃናት የሆድ ቁርጠት (Infantile colic) ምንድን ነው?

የህፃናት የሆድ ቆርጠት የሚታወቀው የልጆቹ እድሜ 6 ሳምንት እና ከዛ በላይ ሲሆነው መሆኑን ባለሙያው ይናገራሉ፡፡
ከ3-4 ወር ባለው ጊዜ ውስጥም የመጥፋት እድል ይኖረዋል፡፡
አንድ ህፃንም የሆድ ቁርጠት ነው የያዘው ለማለት በቀን ውስጥ ቢያስን ለ3 ሰአት ያለማቋረጥ የማልቀስ ይህ ሁኔታ ደግሞ በሳምንት ለ3 ቀን ሚመጣ ከሆነ ይሄ ስሜት ደግሞ ለ3 ሳምንት የሚቆይ ከሆነ ህፃኑ የያዘው የሆድ ቁርጠት ነው ማለት እንችላል ይላሉ ባለሙያው፡፡

መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው?

የህፃናት የሆድ ቁርጠት መንስኤ በውል ባይታወቅም እንደ ምክንያት ሊነሱ የሚችሉ መላምቶች ግን መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

  • እናትየው ከምትወስደው ምግብ ጋር የተያያዘ
  • ህፃኑ በሚወስዳቸው መድሃኒቶች
  • ከላም ወተት ጋር ተያይዞ የሚመጡ አለርጂኮች
  • በተለያየ ምክንያት አንጀታቸው ሲቆጣ
  • ያለግዜ መወለድ
  • ህፃኑ ጡት በሚጠባበት ግዜ የእናት ጡት እና የልጁ አፍ አቀማመጥ የተስተካከለ ካልሆነ አንጀቱ ውስጥ አየር ሲገባ ሊፈጠር ይችላል፡፡

የሚታዪ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

  • ከፍተኛ የሆነ ለቅሶ እና
  • መነጫነጭ ይጠቀሱበታል

ህክምናዎቹ ምንድን ናቸው?

የጨቅላ ህፃናት የሆድ ቁርጠት አብዛኛውን ግዜ ህክምና እንደማያስፈልገው እና በራሱ ግዜ ሊጠፋ የሚችል መሆኑንም ነግረውናል፡፡
ነገር ግን የሚያስፈልገው እናትየውን ማረጋጋት ፣የምታጠባበትን መንገድ ማስተካካል እና እናትየው የምትወስድው አለርጂክ የሚሆኑ ነገሮች ካሉ እነሱን ማስወገድ ይጠቅማል ፡፡
እንዲሁም ህፃኑ ከእነዚህ ምልክቶች ውጪ የሚያሳይ ከሆነ ግን ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል፡፡
በመጨረሻም የጨቅላ ህፃናት የሆድ ቁርጠት ማንኛውም ህፃን ላይ ሊከሰት የሚችል እና ከግዜ በኋላ የሚጠፋ በመሆኑ እናቶች መጨቅ እንደሌለባቸው ዶ/ር ገስጥ ተናግረዋል፡፡

በሐመረ ፍሬው

ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply