#የጨቅላ ህፃናት መታፈን (perinatal asphyxia)የጨቅላ ህፃናት መታፈን ለከባድ ችግሮች እና ሞት ሊዳርግ የሚችል መሆኑ ይነገራል፡፡የአለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃም በአለም ዙ…

#የጨቅላ ህፃናት መታፈን (perinatal asphyxia)

የጨቅላ ህፃናት መታፈን ለከባድ ችግሮች እና ሞት ሊዳርግ የሚችል መሆኑ ይነገራል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃም በአለም ዙሪያ በየአመቱ 9 መቶ ሺ ለሚጠጉ ጨቅላ ህፃናት የሞት ምክንያት መሆኑንም መረጃው ያሳያል፡፡

የጨቅላ ህፃናት መታፈን መጠኑ እና አይነቱ ከከባድ እስከ ቀላል ሊሆንም ይችላል፡፡
ታድያ በዚህ ጉዳይ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን የህፃናት እና የጨቅላ ህፃናት ሀኪም ከሆኑት ዶ/ር ገስጥ መታፈሪያ ጋር ጣቢያችን ቆይታ አድርጓል፡፡

#የጨቅላ ህፃናት መታፈን (perinatal asphyxia) ምን ማለት ነው?

በቂ የሆነ ምግብ እና ኦክስጅን ለእያንዳንዱ የሰውነት ክፍል መድረስ ሳይችል ሲቀር መታፈን እንለዋለን ይላሉ ባለሙያው፡፡

በግዜያቸው የሚወለዱ እና ግዜያቸውን አልፈው የሚወለዱ ልጆች ለመታፈን ችግር የመጋለጥ እድል ይኖራቸዋል፡፡

#መንኤዎቹ ምንድን ናቸው?

#ፅንስ ውስጥ የሚፈጠር የመታፈን ችግር
– የልጆቹ እድገት በቂ ካልሆነ
– እናትዬዋ ላይ የቆየ ጤና ችግር ካለ
– በእርግዝና ግዜ በተለያዩ ምክንያቶች የደም መፍሰስ ከተፈጠረ

#በምጥ ግዜ የሚፈጠር የመታፈን ችግር
– የእናት ማህፀን እና የልጁ ክብደት ካልተመጣጠነ
– የሽርት ውሀ ቀድሞ ከፈሰሰ እና በቂ የሆነ ፈሳሽ ከሌለ

#ከተወለዱ በኋላ የሚፈጠር የመታፈን ችግር ?

ድንገት አንዳንድ ግዜ መጠነኛ የሆነ ችግር ኖሮባቸው ኦክስጅን ወይም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማግኘት ሲኖርባቸው ማግኘት ካልቻሉ ይፈጠራል፡፡

#የመታፈን ችግር ምን ሊያስከትል ይችላል?

አዕምሮዋቸው ላይ በሚፈጠር ችግር መሰረት በማድረግ በደረጃ ይከፋፈላሉ፡፡
እረዥም ግዜ ያልቆየ(ደረጃ 1) የመታፈን ችግር ከሆነ በ 24 ሰዓት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ማገገም የሚችሉበት ሁኔታ አለ፡፡

የሞት ምጣኔያቸውም በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የመታፈን ደረጃው ከፍ ያለ(ደረጃ 2) ከሆነ ግን የሞት መጠኑ ከ20 እስከ 30 ፐርሰንት ከፍ ሊል ይችላል፡፡

ደረጃው ግን ከዚም ከፍ ብሎ (ደረጃ 3) ከሆነ ብዙዎቹ ልጆች ወይም 80 ፐርሰንት የሚሆኑት ልጆች የመሞት እድላቸው ከፍ ያለ እና የአካል እና የአዕምሮ ውስንነት ወይም ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

አንድ ልጅ ታፈነ ማለት ኦክሲጅን ለእያንዳንዱ የሰውነት ክፍል አልደረሰም ማለት ስለሆነ ሁሉም የሰውነታችን ክፍል ተጋላጭ ነው ፡፡
በዋናነት ግን በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳው አዕምሯችን መሆኑን ዶ/ር ገስጥ ተናግረዋል፡፡

#ለመከላከል ምን ማድረግ አለብን ?

– የእርግዝና ክትትል ማድረግ
– የተራዘመ ምጥ እንዳይኖር አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ
– የልጁን የእድገት እና የማህፀን ሁኔታን መገምገም ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

#የሚደረጉ ህክምናዎች ምንድን ናቸው?

– የመጀመሪያው እና ዋናው መተንፈስ የማይችል ልጅ እንዲተነፍስ ማገዝ / መርዳት
– ሙቀት ክፍል በመውሰድ እንዳስፈላጊነቱ የእናት ጡት ወተት በቱቦ መስጠት
– ኦክሲጅን ተመጥኖ በበቂ ሁኔታ መስጠት
– ለህፃኑ ሙሉ ክትትል ማድረግ እንደሚጠቀሱበት ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ይህ ችግር አንዳይከሰት ለመከላከል አንዲት እናት ነፍሰጡር ከሆነችበት ግዜ ጀምሮ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ እና በሚወልዱበት ግዜም የጤና ተቋም ሄደው የሚወልዱበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አስንተዋል፡፡

እንዲሁም እያንዳንዱ የጤና ተቋም ማንኛውም ልጅ ይህ ችግር ሊገጥመው ስለሚችል የተሟላ ግብአት እና የሰው ሀይል አሟልተው መያዝ እንዳለባቸው ዶ/ር ገስጥ ተናግረዋል፡፡

በሐመረ ፍሬው

ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply