
የጸጥታ አካላት ወጣቶች ከጎጃም መስመር ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ቀጥለዋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚያስገባው የጎጃም መስመር፣ አሁንም ድረስ በርካታ ወጣቶች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እየተመለሱ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ ጎሃፅዮን ከተማ መግቢያ ላይ ባለ ኬላ በሚደረግ ፍተሻ ወጣቶች ወደ መጣችሁበት ተመለሱ እንደሚባሉ ተነግሯል፡፡ የአዲስ ማለዳ ዘጋቢ ጥር 15/2015 በቦታው ላይ ተገኝቶ እንደተመለከተው፣ በተለይም ከጎጃምና ከጎንደር የሚመጡ መንገደኞች በቦታው ከአንድ ሠዓት በላይ ለፍተሻ የሚቆሙ ሲሆን፣ የአማራ ክልል የነዋሪነት መታወቂያ የያዙ በርካታ ወጣቶች ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ኬላው ላይ የሚገኙ አብረቅራቂ መለዮ የለበሱ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች፡፡ እነዚህ የጸጥታ ኃይሎች ከአማራ ክልል በጎጃም መስመር ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ወጣቶች፣ ለምን ወደ አዲስ አበባ መግባት ተከለከሉ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡ ወጣቶች ወደ አዲስ አበባ መግባት አትችሉም የሚል አጭር ትዕዛዝ በማስተላለፍ፣ የአዲስ አበባ የሥራ መታወቂያ የያዙ ወጣቶችን ጭምር ወደ መጡበት እንዲመለሱ ሲያደርጉም አዲስ ማለዳ ተመልክታለች፡፡ አዲስ ማለዳ በቦታው በተገኘችበት ስዓትም፣ ከኹለት መኪናዎች 36 እንዲሁም 12 በድምሩ 48 ወጣቶች ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጉን ለማየት ችላለች፡፡ በተለምዶ ታታ ተብለው በሚጠሩ አገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ መኪናዎች ላይ የሚደረገው ፍተሻ ጠንክር ያለ ሲሆን፣ ወጣቶች በብዛት የሚመለሱትም ከእነዚህ መኪናዎች መሆኑን አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው አሽከርካሪዎች ተረድታለች፡ ከጎሃፅዮን እስከ አዲስ አበባ ባለው መንገድ ቀድሞ ያልነበሩ በርከት ያሉ ኬላዎች ተዘርግተው እየተሰቃየን ነው የሚሉት መንገደኞች፣ በቅርቡም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያለበት ልብስ የለበሱ ሰዎችን ከመኪና አስወርደው ሲያስቀሩ ተመልከተናል ብለዋል፡፡ ተጓዦቹ በተደጋጋሚ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት እንዲያስጠብቅ፣ በአገራችን የመንቀሳቀስ መብታችንን እንዲያስከብር ብንጠይቅም የሚሰማን አጥተናል ብለዋል፡፡ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ወጣቶች መግባት አይችሉም የሚለው ክልከላ ብዙ ቀናትን እንዳስቆጠረ በማንሳትም የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ያለአግባብ መገደብ መቆም አለበት ብለዋል፡፡ ዘገባው የአዲስ ማለዳ ነው።
Source: Link to the Post