#የፈረንጆቹ “ማርች” ወር የትልቁ አንጀት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ነዉ፡፡ይህንን በማስመልከት ጣቢያችን ኢትዮ ኤፍኤም 107.8 አጠቃላይ የቀዶ ህክምና እና የትልቁ አንጀት ቀዶ ህክምና…

#የፈረንጆቹ “ማርች” ወር የትልቁ አንጀት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ነዉ፡፡

ይህንን በማስመልከት ጣቢያችን ኢትዮ ኤፍኤም 107.8 አጠቃላይ የቀዶ ህክምና እና የትልቁ አንጀት ቀዶ ህክምና ሀኪም ከሆኑት ከ ዶ/ር ቢንያም ዮሀንስ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

በቆይታችንም ዶ/ር ቢንያም ያነሷቸዉን ነጥቦች በዝርዝር አቅርበንላችኋል፡፡
የትልቁ አንጀት ካንሰር ከአጠቃላይ የካንሰር ዓይነቶች 10 በመቶ ድርሻ በመያዝ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሶስተኛዉ የተለመደ የካንሰር ዓይነት ነዉ፡፡

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በገዳይነቱም በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በከፍተኛ ደረጃ ዕድሜያቸዉ የገፉ ሰዎችን የሚያጠቃ ሲሆን፤በተለይ ዕድሜያቸዉ 50 ዓመት እና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎችን በስፋት ያጠቃል፡፡
የአንጀት ካንሰር በትንሹ አንጀት ፣ በትልቁ አንጀት እንዲሁም በፊንጢጣ ላይ የሚከሰት የካንሰር ህመምን ያጠቃልላል።

#በሀገራችን ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

በወንዶች ላይ እንደአዲስ ከሚታወቁ (newly diagnosed) የካንሰር አይነቶች መሀከል በአንደኛነት እንዲሁ በሴቶች ላይ ደሞ( ከጡትና ከ ማህጸን በር ካንሰር በመቀጠል) በሶስተኛ ደረጃነት ይገኛል።

በአጠቃላይም በሀገራችን በ2020 አውሮፓውያን አቆጣጠር #6ሺህ50 የሚሆኑ አዳዲስ የትልቁ አንጀት ካንሰር ታማሚዎች ተገኝተዋል። ይህም አሀዝ በሚቀጥሉት አመታት እንደሚጨምር ይጠበቃል።

#ለትልቁ አንጀት ካንሰር ምን ያጋልጠናል?

1.የመጀመሪያዉ እድሜ ነዉ፡፡
የአንጀት ካንሰር እድሜያቸው ከ50 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ የመከሰት እድሉ ከፍ ይላል፤ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የአንጀት ካንሰር በወጣቶችና በጎልማሶች ላይም ቁጥሩ እየጨመረ ይገኛል፡፡

በአገራችን በሚገኝ አንድ ሆስፒታል በተሰራ ጥናትም #40በመቶ የሚሆኑት የትልቁ አንጀት ካንሰር ታማሚዎች እድሜያቸው ከ40 አመት በታች ነው ፤ይህም ከሌሎች የአለም ሀገራት በጣም የተለየና የትልቁ አንጀት ካንሰር በአገራችንና ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት በብዛት በጎልማሶች ላይ የመከሰት እድሉ ከፍ ያለ መሆኑን ያሳያል፡፡

2.ሁለተኛዉ ምክንያት የቤተሰብ ታሪክ ነዉ፡፡
የትልቁ አንጀት ካንሰር ወይም የሌላ የሰውነት ክፍል ካንሰር በቤተሰብ ውስጥ የተከሰተ ከሆነ ሌሎች የቤተሰብ አባላት ላይ ወደ ፊት የመከሰት ዕድሉ ከፍ ይላል፡፡

3. የቅድመ ካንሰርነት ደረጃ የደረሱ አንጀት ላይ የሚከሰቱ እባጮች (colonic polyps) ሌላ የሚነሱ ምክንያቶች ናቸዉ፡፡

4. ሌላኛዉ ምክንያት ደግሞ ለካንሰር አጋላጭ የሆኑ የዘረመል ለውጦች መኖር ነዉ፡፡

5. ረጅም ጊዜ የቆዩ የአንጀት ቁስለት ህመሞች (inflamatory bowel disease) ብዙ ጊዜ ችላ እያልን የማንታከማቸዉ ዓይነት ህመሞች፡፡

6. የእንስሳት ተዋጽኦ የሆኑ ምግቦችን ማዘውተር፤ እንደ አትክልት እና ፍራፍሬ ያሉ ምግቦች ገበታችን ላይ አለመኖር ለአንጀት ካንሰር መነሻ ሌላኛዉ ምክንያት ነዉ፡፡

7. ሲጋራ ማጬስና አልኮል አብዝቶ መጠቀም፤ ይህን ማድረግ ለትልቁ አንጀት ካንሰር ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የካንሰር ዓይነቶች የመጋለጥ ዕድላችንንም ከፍ የሚያደርግ ነዉ፡፡

8. ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት፤ ይህ ችግር ለመተንፈሻ አካላት ህመም፣ ለልብ፣ ደም ግፊት እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮችም የሚያጋልጥ ነዉ፡፡

9. አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ፤ አጫጭር መንገዶችን በእግር ከመጓዝ ይልቅ ረጅም ሰዓት ተሰልፎ ትራንስፖርት መጠበቅ፣ በደረጃ መዉጣት የምንችላቸዉን ቦታዎች ቆሞ ሊፍት መጠበቅ እነዚህም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር የሚነሱ ጉዳዮች ናቸዉ፡፡

#ምልክቶቹስ?

የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ የሆድ መነፋት፣ሰገራን እና ፈስን እንደተለመደው ሁኔታ ለማውጣት መቸገር፤ በፊንጢጣ በኩል ደም መፍሰስ፣ መጸዳጃ ቤት ከሄዱ በኋላ ያለመጨረስና የማስማጥ ስሜት፣ በተደጋጋሚ የደም ማነስ ህመም መከሰት፣ ደረጃው ከፍ እያለ ሲሄድም የአንጀት ሙሉ በሙሉ መዘጋትን ሊያመጣ ይችላል፡፡

ምንም አይነት አጋላጭ ነገር ከሌለን ታዲያ የመያዝ ዕድላችን ምን ያህል ነዉ?
ምንም አይነት ለአንጀት ካንሰር አጋላጭ ህመም ወይም ባህሪ ከሌለን በህይወት ዘመናችን በ አንጀት ካንሰር የመያዝ እድላችን ወደ 4% አካባቢ ነው ይህም ለሁለቱም ጾታዎችን ተቀራራቢ ነው።

#እንደ ቅድመ መከላከል ምን እናድርግ?

1. እድሜው/ዋ ከሀምሳ አመት በላይ የሆነ ሰው ወይም አጋላጭ ነገሮች ያሉት/ያላት አልያም ከላይ የተገለጹት ምልክቶች ካሉ አለመዘናጋትና በአፋጣኝ ወደሀኪም ቀርቦ መመርመር ያስፈልጋል።

በሚያስቆጭ ሁኔታ አብዛኛዎቹ ታካሚዎቻችን የአንጀት ካንሰር ህመም ምልክቶች ከታዩ በኋላ ወደ ህክምና ዘግይተው እና ማዳን የማይቻልበት ሁኔታ ላይ ወደ ሀኪም ይመጣሉ የሚሉት ዶ/ር ቢንያም፤ ከተለመዱት የመዘግየት ምክንያቶችም አሜባ ወይም የፊንጢጣ ኪንታሮት ተብለው በተደጋጋሚ መታከም አልያም እንደአማራጭ የተለያዩ መፍትሄዎችን መፈለግ ነው ይላሉ።

2. መቀየር የሚችሉ አጋላጭ ባህሪያት ካሉ ማስተካከል። ቀደም ብለን ያነሳናቸዉን እንደ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ አብዝቶ መመገብ፣ ሲጋራ ማጬስ ፣ አልኮል መዉሰድ የሚሉት ጉዳዮች ማስተካከል የሚችሉ ባህሪያት በመሆናቸዉ ይህን ማረቅ ይገባል፡፡

3. ህመሙ ከታወቀ በኋላ ደግሞ ከሀኪም ጋር ተመካክሮ በቀጣይ ህክምናዎችን በአግባቡ መከታተል አስፈላጊ ነዉ።

በእስከዳር ግርማ
የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply