የፋናን 25ኛ አመት ምክንያት በማድረግ የአፋን ኦሮሞ የስርጭት ጊዜ ላይ የሚያተኩር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

የፋናን 25ኛ አመት ምክንያት በማድረግ የአፋን ኦሮሞ የስርጭት ጊዜ ላይ የሚያተኩር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባለፉት 25 ዓመታት የአፋን ኦሮሞ የስርጭት ጊዜ ላይ የሚያተኩር የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው፥ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የዛሬ 25 አመት አፋን ኦሮሞ ቋንቋን የጀመረ ብቸኛ ሚዲያ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ከዋናው ጣቢያ የስርጭት ሰዓት በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል አምስት የኤፍ ኤም ጣቢያዎች በመክፈት ለህዝቡ ይበልጥ ተደራሽ መሆን መቻሉንም አንስተዋል፡፡

ተቋሙ ባለፋት 25 ዓመታት የኦሮሞ ቋንቋ፣ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ታሪክ እንዲጎለብት አይነተኛ ሚና ተጫውቷልም ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የፌደራል የፍትህና የሕግ ምርምር እና ስልጠና ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር እና የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቦርድ አባል አምባሳደር ደግፌ ቡላ በበኩላቸው፥ ፋና የሀገሪቱ ህዝቦች ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ፣ ዘመናዊ አኗኗርን እንዲከተሉ እንዲሁም ልማት እና ዴሞክራሲ እንዲሠፍን ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

በመድረኩ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ምሁራን ተገኝተዋል፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በ25 ዓመታት ጉዞው የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ስርጭቱ በቋንቋ፣ ባህል አና ስነ ጥበብ እድገት እንዲሁም ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያበረከተው አስተዋጽኦ ላይ የሚያተኩር ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል፡፡

ፋና በቀጣይ ጊዜያት በዘርፉ የተሻለ ስራዎችን ይዞ በመቅረብ እና የአድማጭ ተመልካቾችን ፍላጎት ለማርካት በሚወስዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች ሊተኮርባቸው የሚገቡ ጉዳዮችም በጥናታዊ ጽሁፉ ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ መንግስት ኮሙኑኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ በቋንቋው መረጃ እንዲያገኝ ፋና ለሰራው ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በማርታ ጌታቸው

The post የፋናን 25ኛ አመት ምክንያት በማድረግ የአፋን ኦሮሞ የስርጭት ጊዜ ላይ የሚያተኩር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply