“የፋኖ ኮማንዶዎች፣ የጀኔራል ተፈራ ማሞን መልዕክት ይዛችሁ ሂዱ” #እስክንድር ነጋ የዐማራ ፋኖ በይፋት (ማጀቴ) ምርቃት በድቀት እየተካሄደ ነው። በምርቃቱ የማጀቴ ከተማ ሕዝብ በተለይም ወጣ…

“የፋኖ ኮማንዶዎች፣ የጀኔራል ተፈራ ማሞን መልዕክት ይዛችሁ ሂዱ” #እስክንድር ነጋ የዐማራ ፋኖ በይፋት (ማጀቴ) ምርቃት በድቀት እየተካሄደ ነው። በምርቃቱ የማጀቴ ከተማ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ በነቂስ ተገኝቷል። በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ ምሁራዊ ንግግር ያደረጉት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ፕሬዚደንት እስክንድር ነጋ ወያኔ ለዳግም ጦርነት ገፍቶ የሚመጣ ከሆነ ከጀግናው የአማራ ፋኖ ጋር ወደ ጦር ግንባር እንደሚዘምቱ ቃል ገብተዋል። የአማራ ልዩ ሃይል አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ ከፍትሕ መፅሔት ጋር በነበራቸው ቆይታ ወያኔ በድጋሜ ለመውጋት እየተዘጋጀ መሆኑን መጥቀሳቸውን ያስታወሱት ፕሬዚደንቱ “የፋኖ ኮማንዶዎች፣ የጀኔራል ተፈራ ማሞን መልዕክት ይዛችሁ ሂዱ። ሕወሓት ለዳግም ጦርነት ገፍቶ የሚመጣ ከሆነ እናንተ ብቻ… አይደላችሁም የምትዋጉት። እኔም ቃል እገባላችኋለ። ከጎናችሁ ነኝ። ስንታየሁ ቸኮል እንዳለው እኛም አዲስ አበባ ብንሆንም ፋኖዎች ነን” ብለዋል። በአለፈው ጦርነት አማራ ሳይዘጋጅና ሳይሰለጥን መወጋቱን ጠቅሰው አሁን ግን “ሕወሓት ቢመጣ ይሄን የሰለጠነ ኮማንዶ ሊያልፍ አይችልም። በይፋት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የአማራ አካባቢዎች ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል” ሲሉም ጨምረዋል። በማያሸንፉት ጦርነት ሕዝባቸውን ማስጨረስ እንደሌለባቸውም የትግራይ ወራሪ ሃይል መሪዎችን መክረዋል። ከወያኔ በተጨማሪ አማራን በየቦታው በጅምላ ለሚጨፈጭፈው ኦነግ/ሸኔም ተመሳሳይ ወታደራዊ ዝግጅት መደረግ እንዳለበት ፕሬዚደንቱ አሳስበዋል። “በርግጥ ኦነግ ሸኔ የፈሪ ሰራዊት ነው። ፈሪ ነው ሕፃናትንና እናቶችን የሚያርደው” ሲሉም ገልፀዋል። ይሄ ዛሬ ለምርቃት የበቃው ስልጠና በቁጥሩና በሥልጠና ጥራቱ መጨመር እንዳለበትም ጠቅሰዋል። የባልደራስ የአደረጃጀት ጉዳዮች ሓላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል “ሰሞኑን ከወለጋ ተፈናቅለው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ እየተሳደዱ ያሉ አማሮች አሉ። ይህን ዩኒፎርም የለበሳችሁ ፋኖዎች የእነዚህ አማሮች አለኝታ ናችሁ። በየቦታው እየወደቁ ላሉ አማሮች አለኝታ ናችሁ። እኛም ፋኖዎች ነን። ሰልጣኞች ነን” ብለዋል በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ስሜት ቀስቃሽ ንግግር። በተጨማሪም እስክንድር ነጋ “ፋኖ ሀገር ማዳን አለበት። የሚያድነው ግን በማንነታችን እንድንጨፈጨፍበት አይደለም። በመከላከያ ተስፋችን አልተሟጠጠም። ነገር ግን ሙሉ ተስፋ አናደርግበትም። ይህን እኛ ስንለው ነበር፤ ጀኔራል ተፈራ አረጋግጠውልናል። ልዩ ሃይሉ ላይም ተመሳሳይ ችግር አለ። ሙሉ ተስፋ የሚጣልበት ፋኖ መሆኑን ጀኔራል ተፈራ ማሞ ተናግረዋል። ይሄን እኔ ብቻ አይደለሁም የምለው። አማራ በራሱ አቅም ራሱን መቻል አለበት። ሌሎች እንዲወስኑለት መጠበቅ የለበትም። ይህንንም ያሉት ጀኔራል ተፈራ ናቸው። ፋኖን በተገቢው መንገድና ስነ ምግባር ማደራጀት ያስፈልጋልም ብለዋል። ሌላ መጨመር አያስፈልግም። ይህንን የተፈራን መልዕክት ይዘን ወደ ቤታችን እንሂድ” በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል። በአካባቢው የፋኖ አደረጃጀት አስተባባሪ የሆኑት አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ አሰግድ መኮንን በበኩላቸው የአማራን አንድነት ማስጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። “አሁንም እንዳንደራጅ፤ እንዳንሰለጥን ብዙ ችግሮች አሉ። ዛሬም አንድ እንዳንሆን ይከፋፍሉናል። ውርደትን ካባ ያደረጉ ሰዎች ናቸው የሚለያዩን። ተንኮለኛም ቢሆኑ ግን ከቶ በክፉ አንመለከታቸውም። ይበልጥ አንድ መሆን አለብን” ብለዋል። ለፋኖ ወታደራዊ የስነ ምግባር መመሪያ ያሉትንም በዝርዝር አቅርበዋል። ከመርሆዎቹ መካካል ጨዋነት፣ ታማኝነት፣ ኢ-ህንዝላልነት፣ ምስጢራዊ ሰነዶችን ጠባቂነትን እና ሌሎይንም ዘርዝረዋል። በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ ወኔ ቀስቃሽ የሙዚቃ ዝግጅቱን ያቀረበው ተወዳጁ ድምፃዊ አሸብር በላይ በበኩሉ “በአራቱም አቅጣጫ ያለ አማራ የሚያቆመው የለም። አንድ መሆን አለበት። በተለይ ወጣቱ መጠንከር አለበት። ኢትዮጵያን የሚታደገው ይህ ነው” ብሏል። መርሃ ግብሩ በተለያዩ የመዝናኛና የገቢ ማሰባሰቢያ ክንውኖች እንዲሁም ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮች እንደቀጠለ ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply