‹‹የፌደራሉ መንግስት ለኢንተርፕራይዞቹ ስራ መጀመር ምንም ዓይነት ድጋፍ አላደረገም›› የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጥር 28 ቀን 2016 በሕዝብ ተወካዮች ምክር…

‹‹የፌደራሉ መንግስት ለኢንተርፕራይዞቹ ስራ መጀመር ምንም ዓይነት ድጋፍ አላደረገም›› የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጥር 28 ቀን 2016 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ‹‹ከ200 በላይ ኢንዱስትሪዎች ስራ ጀምረው ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው›› ብለው እንደነበር ይታወሳል፡፡

‹‹የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ መጀመር የፈጠረላቸዉ ዕድል እንጂ ኢንተርፕራይዞቹን ወደ ስራ ለመመለስ በመንግስት ደረጃ ታቅዶ ፣ የራሱ በጀት እና አሰራርን ተከትሎ የተደረገላቸዉ ምንም ዓይነት ድጋፍ የለም›› ሲሉ የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ገ/ጻድቅ ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል፡፡

‹‹ወደ ስራ ገብተዋል የተባሉት ኢንተርፕራይዞች ቁጥር ትክክል ነዉ ፤ ሪፖርትም የተደረገዉ ከእኛ ነዉ ነገርግን ከፌደራሉ መንግስት የተደረገላቸዉ ምንም ዓይነት ድጋፍ የለም፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ስንሰማ እኛም ኢንተርፕራይዞቹም ላይ ነዉ ግርምት የተፈጠረዉ›› ብለዋል፡፡

ለዚህም እንደማሳያነት የገለጹት ከዛሬ 11 ወራት ገደማ በፊት ወደ 1መቶ39 የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች የሚያስፈልጋቸዉ ድጋፍ ከተደረገላቸዉ ከ 2 ሳምንት እስከ 6 ወራት ባለዉ ጊዜ ዉስጥ ወደ ስራ እንደሚገቡ ቃል መግባታቸዉን በመግለጽ ለፌደራል መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸዉ ሪፖርት መደረጉን ነዉ፡፡

‹‹ነገርግን እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ድጋፍ የተደረገላቸዉ ኢንተርፕራይዞች የሉም››፤ ወደ ስራ የተመለሱትም በራሳቸዉ ጥረት እንጂ በማንም ድጋፍ አይደለም ሲሉ አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ቀርበዉ የተናገሩት ‹‹የተሟላ ድጋፍ ተደርጎላቸዉ ወደ ስራ ተመልሰዋል››የሚለዉ ንግግር በአጠቃላይ ስህተት ነዉ ፡፡ ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታም ያላገናዘበ ግምገማ ነዉ የተደረገዉ›› ሲሉ አቶ ዳዊት ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

በሙሉ አቅማቸዉ እየሰሩ ባይሆንም ግን ወደ ስራ ተመልሰዋል ከተባሉት 2መቶ17 ኢንተርፕራይዞች /አምራቾች/ መካከል 202 አነስተኛ ፣ 5 መካከለኛ ፤ 12 ደግሞ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ናቸዉ፡፡

እስከዳር ግርማ
የካቲት 07 ቀን 2016 ዓ.ም

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ወቅታዊ አዳዲስ መረጃዎችና ፕሮግራሞችን ለማግኘት ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

Twitter https://twitter.com/EthioFM

YouTube https://www.youtube.com/@onelovebroadcast/videos

Facebook https://www.facebook.com/onelovebroadcast

Source: Link to the Post

Leave a Reply