You are currently viewing የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ማሻሻያ “ለአግላይነት ክፍት ነው” የሚል ትችት ቀረበበት   

የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ማሻሻያ “ለአግላይነት ክፍት ነው” የሚል ትችት ቀረበበት   

በናሆም አየለ

የመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ የብሔር ብሔረሰቦች “ብዙሃነት እና አካታችነትን” ያገናዘበ ስርዓት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚደነግገው የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ማሻሻያ፤ “ለአግላይነት ክፍት ነው” የሚል ትችት ቀረበበት።  በፌደራል ደረጃ “አንድም ሰራተኛ የሌላቸው 17 ብሔር ብሔረሰቦች” እንዳሉ የገለጸው የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፤ የወደፊት ቅጥሮች “ይህን ታሳቢ ማድረግ አለባቸው” ብሏል።

በፌደራል መንግስት ሰራተኞች የአዋጅ ረቂቅ ላይ የቀረቡ ትችት እና ጥያቄዎች የተስተናገዱት፤ በተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጠራው የህዝብ ይፋ ውይይት ላይ ነው። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን (ኢሰመኮ) በመወከል በውይይቱ የተሳተፉት ሰዊት ዘውዱ፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ “ኢትዮጵያን የሚመስል ተቋም” መገንባትን በተመለከተ ስለተቀመጠው ድንጋጌ ጥያቄ አቅርበዋል። 

“የብሔር ስብጥርን ማካተት ከዚህ ውስጥ አንዱ የተነሳው ነው። ይህ ለአግላይነት ክፍት የሚሆንበት እድል ሰፊ ስለሆነ፤ አዋጁ ምን አይነት የቁጥጥር ስርዓት አበጅቷል?” ሲሉ በኢሰመኮ የህግ ባለሙያ የሆኑት ሰዊት ጠይቀዋል። እርሳቸው የጠቀሱት የአዋጁ ድንጋጌ “በማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ኢትዮጵያን የሚመስል የመንግስት ሰራተኞች ስብጥር መኖሩን በማረጋገጥ፤ የብሔር ብሔረሰቦችን፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የጾታ ተዋጽኦ የመሳሰሉትን ብዙሀነት እና አካታችነትን ያገናዘበ የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ መደረግ አለበት” ይላል። 

ፎቶ፦ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥታ ስርጭት የተወሰደ

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ መምጣታቸው የገለጹት አቶ አብርሃም ገድፍ የተባሉ ተሳታፊም፤ የብሔር ብሔረሰቦች “ብዙሃነት እና አካታችነት” ስርዓትን በተመለከተ ተጨማሪ ጥያቄ ሰንዝረዋል። በቢሮው የሰው ሃብት ስራ አመራር፣ ክትትል እና ድጋፍ መሪ የሆኑት አቶ አብርሃም፤ በአዋጁ የተጠቀሰው ስርዓት “በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ታች ባለው [ባለሙያ] ደረጃ እንዲካተት መደረጉ፤ ብቃት የምንለውን፣ ባለሙያነት የምንለውን ችግር ውስጥ አይከተውም ወይ?” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። 

ለስድስት ዓመታት ያህል በስራ ላይ የቆየውን የመንግስት ሰራተኞች አዋጅን እንዲተካ በተዘጋጀው በአዲሱ የህግ ረቂቅ ላይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች “ብቃት እና ውድድርን መሰረት በማድረግ” የሰራተኞች ስብጥር እንዲኖር የሚያስችሉ ዕቅዶችን መተግበር እንዳለባቸው ተቀምጧል። መስሪያ ቤቶቹ ይህን ለማድረግ የሚያስችል “የክትትል እና የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንደሚኖሮባቸውም” በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

“ብቃት እና ውድድርን መሰረት ማድረግ” የሚለው አገላለጽ፤ “አነስተኛ ብሔራዊ ተዋጽኦ” ስላላቸው ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተጠቀሰበት የአዋጁ ክፍል ላይም ተጠቅሷል። “በመንግስት መስሪያ ቤት የሚፈጸም የሰራተኛ ስምሪት፤ የብሔር ብሔረሰቦችን እና ህዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጽኦ ለማሳደግ የሚያስችሉ እቅዶችን በመተግበር፤ ብቃት እና ውድድር መሰረት ተደርጎ መፈጸም አለበት” ሲል የአዋጅ ረቂቁ ያዝዛል።

ፎቶ፦ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥታ ስርጭት የተወሰደ

በፓርላማ የህዝብ ውይይት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አመራሮች አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ስመኝ ውቤ፤ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ሀገር በመሆኗ ይህንኑ ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። “ብዝሃነትን እንድናስተናግድ ግድ የሚሉን እውነታዎች አሉን። ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ሀገር ናት። ስለዚህ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች [መገኛ] በሆነች ሀገር፤ ምንም አይነት የመንግስት ሰራተኛ የሌላቸው ብሔሮች መኖር ተቀባይነት የለውም” ብለዋል። 

በፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ወ/ሮ ስመኝ፤ “ለምሳሌ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በፌደራል ደረጃ ወደ 17 የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች አንድም ሰው፣ [አንድም] ሰራተኛ የሌላቸው አሉ። በተለይ አሁን ባለው ሁኔታ አብዛኞቹ እየተማሩ ስለሆነ፤ ወደፊት የመንግስት ሰራተኛ ቅጥር ሲካሄድ ከእነኚህ የተማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ ቅጥር ሊኖር ይገባል። ይህ ግን ‘ሜሬትን’ ወይንም ብቃትን መተካት የለበትም የሚል ነው በግልጽ የተቀመጠው” ሲሉ አብራርተዋል።

የተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፤ “የአካታችነት፣ የብዝሃነት ጉዳይ” በአዋጁ የተካተተው “ችግር ስላለ፤ መፍትሄ ስለሚያስፈልገው” መሆኑን ተናግረዋል። “አንዳንዶች በተለያየ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንደሚያነሱት አይደለም። አንዱን አውጥቶ ሌላውን መተካት አይደለም” ሲሉም የቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢው የአዋጅ ረቂቁን ተከላክለዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ዶ/ር ነገሪ “ብዙሃነት፣ አካታችነት እና ‘ሜሬት’ አብሮ ይሄዳል ወይ?” በሚል ለሚነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል። “መሳሳት የለብንም። ብቃት፣ ‘ሜሬት’ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ብሔሮች ጋር አለ። እንደ ሀገር መሪ ማሰብ ያለብን ‘እንዴት ሁሉም እድል አግኝቶ ሀገሩን ማገልገል ይችላል’ [ነው]። ብቃቱ እኮ ተፈጥሯል። የትምህርት ተቋማት ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር በየአካባቢው እንዲስፋፉ የተደረገው፤ በሁሉም ዞኖች ባይሆኑም በአቅራቢያቸው ዜጎቻችን እየሰሩ እራሳቸውን እንዲያሻሽሉ ታስቦ ነው” ሲሉም የቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አስገንዝበዋል። 

ከሶስት ሳምንት በፊት ለፓርላማ በቀረበው የፌደራል መንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ ላይ፤ ወደፊትም ተጨማሪ የውይይት መድረኮች እንደሚኖሩ ዶ/ር ነገሪ ጠቁመዋል። በነገው ዕለት “አጠቃላይ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚሳተፉበት መድረክ ስለሚኖረን፤ የተሻለ ግብዓት እናገኛለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

Source: Link to the Post

Leave a Reply