የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህወሀትን ቡድንን እና የኦነግ ሸኔን የጥፋት ተልዕኮ ይዘው ተንቀሳቅሰዋል በሚል የጠረጠራቸውን ከ93 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።ኮሚሽኑ ባለፉት 15…

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህወሀትን ቡድንን እና የኦነግ ሸኔን የጥፋት ተልዕኮ ይዘው ተንቀሳቅሰዋል በሚል የጠረጠራቸውን ከ93 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ባለፉት 15 ቀናት ውስጥ የህወሀት እና ኦነግ ሸኔ የጥፋት ተልዕኮ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ93 በላይ ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።

ኮሚሽኑ ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ጦርነቱን አዲስ አበባ ጀምረን አዲስ አበባ እንጨርሳለን ብሎ ሀገር የመናድ ጦርነት የለኮሰው ወንበዴው፣ አሸባሪውና የማፊያዎች ስብስብ የሆነው የህወሀት ጁንታ ቡድን ከዕለት ዕለት ወታደራዊ ሽንፈትና ክሽፈት እየተከናነበ ይገኛል ብሏል።

ጽንፈኛው ቡድን በከፈተው በዚህ ባልተጠበቀ ጥቃት እንደመከላከያ ሰራዊታችን ሁሉ በትግራይ ክልል የሚገኙ ከ22 በላይ የልማት አውታሮችን ከየትኛውም ጥቃት ሲጠብቁ አመታትን ባስቆጠሩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ አባላት መኖሪያ ካምፖች ላይ ጥቃት በማድረስ በርካታ አባላት ላይ የግድያና የአፈና ወንጀል መፈጸሙን የኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ጄይላን አብዲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት በከፍተኛ ቁጭትና ወኔ በመነሳሳት በመሃል ሀገር ያለውን የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ ቀን ከሌት በትጋት ሙያዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

ይህ የጥፋት ቡድን አባላትና ተላላኪዎቻቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፣ በቦሌና በየክልሉ በሚገኙ ኤርፖርቶች፣ በዩኒቨርስቲዎች፣ በሀይል ሰብስቴሽኖች፣ በውሃ ግድቦች፣ በነዳጅ ዲፖዎች፣ በፋብሪካዎች፣ በድልድዮች፣ በስደተኛ ካምፖች፣ በሳተላይት ጣቢያዎች፣ በማዕድን ማውጫዎች፣ በቤተመንግስትና በክልል ም/ቤቶች፣ በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች፣ በልማት ድርጅቶች፣ በዋና ዋና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች፣ በምድር ባቡር ፕሮጀክቶች፣ በቢሮዎችና መኖሪያ ካምፖች፣ በፌዴራል ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች እንዲሁም ሌሎች የልማት አውታሮችና ጠረፍና የጠረፍ ከተሞች ላይ ሊሰነዘሩ የሚችሉትን ጥቃቶች አስቀድሞ ለማክሸፍ ጥብቅ ክትትልና ቋሚ ጥበቃ በማድረግ ላይ ይገኛሉም ብሏል፡፡

ከዚህም ባለፈ በግዳጅ የነበሩት የፌዴራል ፖሊስ አባላት የከሃዲው ህወሀት ቡድንን ጥቃት በመከላከል በአንዳንድ ግንባሮች ከጀግናው ሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ጎን በመሆን በግንባር እየተፋለሙ ይገኛሉም ተብሏል።

ሌሎች ደግሞ በሰሜን ቀጠና፣ በምዕራብ ቀጠና በኦሮሚያ ወለጋ ዞኖች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና መተከል ዞን እና አካባቢው፣ በደቡብ ቀጠና በሚዛን ቴፒ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በወላይታ ሶዶ እና ኮንሶ፣ ከነገሌ ቦረና እስከ ሞያሌ፣ በምስራቅ ቀጠና ከአዋሽ እስከ ጋላፊ እንዲሁም በሁሉም የሀገራችን ድንበሮች ከክልሎች የፀጥታ ሀይልና በየቦታው ካለው የመከላከያ ሰራዊታችን ጋር ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠርና የህዝብን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ የህግ የበላይነት እንዲከበር ሌት ተቀን በትጋት እየሰሩ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ከተለያዩ ክልሎች ፖሊስ በዚህ ወንጀል የጠረጠራቸውን ከ93 በላይ የህወሀት ቡድን አባላትና የኦነግ ሸኔ ቡድን አባላትን በህግ ቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሆነ ተገልጿል።

በተደረገ ብርበራ፣ ፍተሻና አሰሳ እንዲሁም በህብረተሰቡ ጥቆማ፡- 30 የመከላከያና የፖሊስ የደንብ ልብስ፣ 47 የተለያዩ ጠመንጃዎች፣ 43 የተለያዩ ሽጉጦች፣ 1 ሺህ 376 የተለያዩ ጥይቶች ፣ 7 ቦምቦች፣ 2 የጦር ሜዳ መነፅር፣ 102 ድምፅ አልባ መሳሪያ፣ 8 የእጅ ራዲዮ መገናኛ፣ ለእኩይ ተግባራቸው ማስፈፀሚያ የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የቴሌኮሚዩኒኬሽን መሳሪያዎች፣ 534 ሺህ 870 የኢትዮጵያ ብር እና የተለያዩ ተሸከርካሪዎች መያዝ ተችሏል፡፡

ይህ የተገኘው ውጤት ሰላም ወዳዱ የሀገሪቱ ዜጋ እና በየክልሉ የሚገኙ የፀጥታ አካላት ከፖሊስ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመስራታቸው የተገኘ ስኬት በመሆኑ ይህንኑ ትብብሩን አጠናክሮ በመቀጠል ለሰላምና ደህንነታችን መረጋገጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት እያሳሰብን በቀጣይ ለሚደረጉ የህግ ማስከበር ተግባራት የተለመደውን ድጋፍና ትብብራችሁን እንጠይቃለን ብሏል፡፡

አጠራጣሪ ነገሮች ሲኖሩ መረጃ ለመስጠት በስልክ ቁጥሮች፦ 987፣ 816 እንዲሁም በ0115-51 80 00 ደውላችሁ አሳውቁኝ ተብላችኋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያን
ሕዳር 12 ቀን 2013 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply