
የፍርድ ቤት የብርበራ ማዘዣ የጠየቁ የሚዲያ ሠራተኞች 8 ቀን በእስር ላይ ሆኖ እንዲመረመሩ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ሰጠ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው ተከራይቶ የሚሰራበት ስቱዲዮ ፀሃፊ ወ/ሮ መሰረት ታምሩ እና የካሜራ ባለሙያ አቶ አማኑኤል አስፋው በባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም ለእስር መዳረጋቸው የሚታወቅ ነው። ወ/ሮ መሰረት ታምሩ እና አቶ አማኑኤል አስፋው የቪዲዮ ቀረጻ አገልግሎት ከሚሰጡበት ድርጅት ፤ የፍርድ ቤት የብርበራ ማዘዣ ፍቃድ የሌላቸው የመንግስት የጸጥታ ኅይሎች ፤ ፍ/ቤት በዋስ እንዲወጣ የፈቀደለትን ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋውን ለፍተሻ እና ብርበራ በሚል ምክንያት ተከራይቶ የሚሰራበት ስቱዲዮ በማስገደድ ብርበራ አካሂደዋል። በድርጅቱ የሥራ ቦታ የነበሩ ሠራተኞች ፤ ፖሊስ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብርበራ አካሂዳለሁ ማለቱ አግባብ እንዳልሆነ እና የፍርድ ቤት ማዘዣ ሊደርሳቸው እንደሚገባ ለጸጥታ ኃይሎች ቢገልጹም ፤ በማስገደድ ብርበራ በማካሄድ ፣ ወ/ሮ መሠረት ታምሩ እንዲሁም አቶ አማኑኤል አስፋው ከላይ በተገለፁት የፀጥታ ሀይሎች ታፍነው ሜክሲኮ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ተወስደው ታስረዋል። የካቲት 13/2015 በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት፤ ከሰዓት በኋላ በዋለው ችሎት ወ/ሮ መሠረት ታምሩ እና አቶ አማኑኤል አስፋው ፤ ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበዋል። ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ከፍቶ ለፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታም ተጠርጣሪዎች በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባት በመጠቀም ፤ 1) ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር ብሔርን ከብሔር በማጋጨት ፣ 2) ሕዝብና መንግስትን ለማጋጨት ፣ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ እያሉ በተደረገ ክትትል በቁጥር ሥር ውለዋል ይላል። “በሰውና በሰነድ ማስረጃ ማጣራት እንድንችል ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ማጣራያ የጊዜ ቀጠሮ ይፈቀድልን” በማለት ፖሊስ ለፍ/ቤት ጥያቄውን አቅርቧል። የታሳሪዎች ጠበቆች በፖሊስ በኩል ለቀረበው አቤቱታ በሰጡት ምላሽ ” ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ጉዳይ የዋስትና መብትን የሚያስከልክል አይደለም” ሲሉ ተከራክረዋል። “ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ሕጋዊ አሰራር እንዲከተል በመጠየቃቸው እንደ አንድ ንቁ ዜጋ የሚያስቆጠር እንጂ ፤ የወንጀል ፍሬ ነገር የሌለው ከመሆኑ ባሻገር በያዛቸው አካል የሚያስመሰግን ድርጊት ከመሆኑ ባለፈ የሚያሳስራቸው አይደለም” ሲሉም አክለዋል። “ከዚህ ጋር ተያይዞ ተጠርጣሪዎች የተያዙት ለምርመራው አጋዥ በሆነ መንገድ ሳይሆን ፤ በሥራ ቦታቸው ላይ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ባሉበት ጊዜ ፖሊስ ለብርበራ መምጣቱን ሲገልጽ የፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ ከያዙ ብርበራ ማድረግ እንደሚችሉ ስለተገለጸላቸው ብቻ ይህንን እንደ ሕገወጥ ተግባር በማየት ደንበኞቻችን አስሮ የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ ሕገመንግስታዊም ፣ ሥነ ሥርዓታዊም ባለመሆኑ ደንበኞቻችችን በዋስ መውጣት አለባቸው ” በማለት ጠበቆች ለፍ/ቤቱ ጠይቀዋል ። ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ለፖሊስ ተጨማሪ 8 ቀን የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ፤ ለየካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ጠዋት 3፡30 እንዲቀርቡ ሲል ተለዋጭ ቀጠሮ ስለመስጠቱ ጋዜጠኛ ይድነቃቸው ከበደ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ አጋርቷል።
Source: Link to the Post