የፒያሣና አራት ኪሎ ነዋሪዎች ለመልሶ ማልማት ሊነሱ ነው

የፒያሣና አራት ኪሎ  ነዋሪዎች ለመልሶ ማልማት ሊነሱ ነው

የፒያሳ ነዋሪዎች በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ አካባቢውን እንዲለቁ ተነግሯቸዋል

በአዲስ አበባ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ፣ የፒያሳና አራት ኪሎ ነዋሪዎች ለልማት ከመኖሪያቸው እንደሚነሱ የክፍለ ከተማው አስተዳደር  ገልጿል።
አስተዳደሩ  በማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ እንዳስታወቀው፤ ሁለቱን አካባቢዎች መልሶ በማልማትና ነዋሪዎችን በማስነሳት ዙሪያ ሰሞኑን  ከነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል። ውይይቱ፣ በንግድ የሚተዳደሩ ነዋሪዎች ንግዳቸውን በሚቀጥሉበትና ሌሎች ነዋሪዎች በመልሶ ማልማቱ ዕቅድ በሚስተናገዱበት ኹኔታ ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል።
ነዋሪዎችን ለልማት የማንሳቱን ሂደት የሚከታተል ከአመራሩና ከነዋሪዎች የተውጣጣ ኮሚቴም እንደተዋቀረ ተገልጧል። በተለይ የፒያሳ ነዋሪዎች በሦስት ወራት ውስጥ አካባቢውን እንዲለቁ እንደተነገራቸው ምንጮች ጠቁመዋል። ነባር ነዋሪዎቹን የማስነሣቱ ስራ በሦስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ የግንባታ ስራው ይጀመራል ተብሏል።በተያያዘ ዜናም፣ ከቀበና እስከ አራት ኪሎ  እንዲሁም  ፒያሳ ደጎል አደባባይ ድረስ  የመንገድ ኮሪደር ግንባታ ሥራው ሠሞኑን  ተጀምሯል፡፡
 የከተማ አስተዳደሩ  ካቢኔ የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው የ3ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ጉባኤ፣ ግንባታቸው እንዲጀመር ውሳኔ ካስተላለፈባቸው አምስት  የከተማዋ የመንገድ ኮሪደሮች መካከል በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘውና  ከቀበና አደባባይ – አራት ኪሎ – ፒያሳ ደጎል አደባባይ ኮሪደር አንዱ ነው።
 የመንገድ ኮሪደር  ግንባታው በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የአራት ኪሎው  ባለፈው ረቡዕ  ተጀምሯል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply