የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ስልጣናቸውን ለመልቀቅ” አስበው እንደሆነ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ላይ ጠይቀዋል።
የፓርላማ አባሉ “በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ እንዲሁም በማንነት ተኮር የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማጽዳት እና የማንነት ማሳሳት ወንጀሎች ተጠያቂ ለመሆን ምን ያህል ዝግጁ ነዎት?” ሲሉም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጨማሪ ጥያቄ አቅርበዋል። አቶ ክርስቲያን በመንደርደሪነት ያነሱትን ነጥብ እና ጥያቄቸው ከዚህ በታች እንደሚከተለው ቀርቧል፦
“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ምክር ቤት እና በተለያዩ መድረኮች ስለእርሶ እና ስለሚመሩት የአስፈጻሚ መንግስት ተጠየቅ ሲቀርብብቦት፤ ለተጠየቁት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጠያቂዎችን የሚያጥላላ አስተያየት ሲያራምዱ፤ አለፍ ሲልም ተጠየቅ የቀረበቦት የወጡበትን ብሔር በመጥላት እንደሆነ አድርገው ምላሽ ሲሰጡ የቅርብ ትዝታችን ነው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጥያቄ የማቀርብልዎ እኔ በብሔሬ አይደለም። ይህንን ጥያቄ ሳቀርብሎት እርሶም የሚወክሉትን ብሔር በመጥላት አይደለም።
ምላሽ እና ማብራሪያ ሲሰጡም ለጥያቄ፤ ብሔርዎን እና ምናልባት ‘የመንግስት ግልበጣ ሴራ ነው’ በሚል ምላሽ እና ማብራሪያ እንዳይሰጡ ከወዲሁ አደራ ማለት እፈልጋለሁ።”
“የዜጎችን ደህንነት እና የሀገርን ሉዓላዊነት መጠበቅ ዝቅተኛ የመንግስት ኃላፊነት ሆኖ ሳለ፤ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ይገደላሉ፣ ይፈናቀላሉ፣ ቤታቸው ይፈርሳል፣ ንብረታቸው ይወድማል።
የሀገር ሉዓላዊነትን በሚዳፈር መልኩ የጎረቤት ሀገራት ሰራዊቶች በኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ወሰኖች በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ዘልቀው በመግባት ወረራ ፈጽመዋል።
ይህ ቀደም ሲል፤ ከእኔ የቀደሙ የተከበሩ የምክር ቤት አባላትም በጥያቄ መልክ ያቀረቡት፣ የኢትየጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም በሪፖርቱ ደጋግሞ፤ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ስለሚገደሉ ዜጎች፣ ስለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ወንጀሎች፣ መፈናቀሎች፣ ግድያዎች፣ ቤት መፍረሶች በሪፖርቱ ያቀረበው ነው።”
“አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የዜጎች ደህንነት እና የሀገር ሉዓላዊነት ዋነኛ ስጋት ምንጭ ሆኖ የምናየው እርሶ የሚመሩትን መንግስት ነው።
እርሶ በአፍዎ ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም’ ቢሉንም፤ በተግባር ግን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በመንግስትዎ እየተናዱ ነው።
የበርካታ ሀገራት መሪዎች መሰል ኃላፊነትን በወጉ ያለመወጣት ጉድለት ሲያሳዩ፤ ህዝብን ይቅርታ ጠይቀው ስልጣናቸውን ሲለቁ ይታያል።
በሀገራችንም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተመሳሳይ ህዝባዊ ተጠየቅ ሲቀርብባቸው ስልጣን መልቀቃቸውን እናስታውሳለን። እርሶም ወደ ስልጣን የመጡት በዚህ ተጠየቅ ምክንያት ነው።
እርስዎስ ስልጣንዎን በመልቀቅ የመፍትሔ አካል ለመሆን አላሰቡም ወይ? በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ እንዲሁም በማንነት ተኮር የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማጽዳት እና የማንነት ማሳሳት ወንጀሎች ተጠያቂ ለመሆን ምን ያህል ዝግጁ ነዎት?” (በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠናቀረ)
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም
ለተጨማሪ መረጃዎች የቴሌግራምና የዩቲዩብ ቻናሎቻችንን ይቀላቀሉ!
Telegram https://t.me/ethiofm107dot8
YouTube https://www.youtube.com/@onelovebroadcast
ያሎትን አስተያየት እና ጥያቄ በአጭር መልዕክት 6321 ላይ ይላኩልን።
ከኛ ጋር ስለሆናችሁ ከልብ እናመሰግናለን
Source: Link to the Post