የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ አገር አቀፍ ፈተና ተጠናቀቀ

አርብ ጥቅምት 11 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኹለት ዙር ሲሰጥ የነበረው የ2014 የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና መጠናቀቁን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በኹለት ዙር ሲሰጥ በነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ 900 ሺሕ በላይ ተማሪዎች በ130 የፈተና ጣቢያዎች ተፈትነዋል።

ፈተናው በመጀመሪያዉ ዙር የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና ሂደት ካጋጠሙና በመጀመሪያዉ ዙር ማጠቃለያ ከተገለጹ ችግሮች ዉጪ በታቀደው መሰረት በስኬት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የኹለተኛ ዙር ተፈታኞችም ከዛሬ ጀምሮ ወደ የአካባቢያቸው መመለስ መጀመራቸው ተገልጿል።

ዩኒቨርስቲዎች ለፈተናው ውጤታማነት ያደረጉት ዝግጅት እና በፈተና አሰጣጥ ሂደት ላይ የነበራቸው አስተዎፆ ከፍተኛ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ ተፈታኞችም የፈተና ስርዓቱን ባከበረ መልኩ ፈተናቸውን ሲወስዱ ቆይተዋል ተብሏል።ለዚህም የትምህርት ሚኒስቴር ለወላጆች፣ ተፈታኝ ተማሪዎች እና ፈታኝ መምህራን ፣ጣቢያ አስተባባሪዎች፣ ሱፐርቨይዘሮች ፣ የጸጥታ አካላት እና በየደረጃው ለፈተናው ስኬታማነት የበኩላቸውን ለተወጡ አካላትም ላቅ ያለ ምስጋናውን አቅርቧል።

የዘንድሮው የፈተና አሰጣጥ ሂደት የፈተና ስርቆት እና ኩረጃን በማስቀረት ሂደት የነበረው አስተዎፆ ውጤታማ መሆኑ የታየበት እንደነበረም ሚኒስቴሩ የገለጸ ሲሆን፤ በቀጣይም የፈተና አሰጣጥ ስርዓቱን በማሻሻል የተሻለ እና በራሱ የሚተማመን ትውልድን ለመፍጠር በትኩረት የሚሰራ ይሆናል ብሏል።የፈተናዉን አጠቃላይ ሂደት በሚመለከት ዝርዝር መረጃዎችን በቀጣይ እንደሚያሳውቅም ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።

The post የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ አገር አቀፍ ፈተና ተጠናቀቀ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply