የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሐምሌ 19 እስከ 30/2015 በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ይሰጣል

ሐሙስ ግንቦት 10 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የ2015 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ማጠቃለያ ፈተና ከሐምሌ 19 እስከ 30/2015 ድረስ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ግንቦት 09/2015 ተፈርሞ፤ ለኹሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ለኹሉም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ለኹሉም የክልል ትምህርት ቢሮዎች የተሰራጨ ደብዳቤ ፈተናው በተጠቀሱት ቀናት እንደሚሰጥ አመላክቷል፡፡

በዚህም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከሐምሌ 15 ቀን 2015 ጀምሮ ብሔራዊ ፈተናውን የመስጠት ሥራ ላይ ብቻ ትኩረት እዲያደርጉ የትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫ ማስቀመጡ ተገልጿል።

በተጨማሪም በ2015 የመውጫ ፈተና ለመውሰድ የተመዘገቡ በግልና በመንግሥት ተቋማት የሚገኙ እጩ ምሩቃን እና ባለፉት ዓመታት የህግ መውጫ ፈተና ወስደው የማለፊያ ውጤት ያላስመዘገቡት ተማሪዎች በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች የመፈተኛ ማዕከላት ውስጥ ፈተናው ከሐምሌ 3 እስከ 13 ባሉት ቀናት ተሰጥቶ እንዲጠናቀቅ ሚኒስቴሩ በደብዳቤው አሳስቧል።

ሚኒስቴሩ አክሎም፤ በ2014 የ12ኛ ክፍል አጠናቀው ፈተና በመውሰድ በልዩ ሁኔታ የሬሜዲያል ኘሮግራም ተጠቃሚ ለሆኑ ተማሪዎች ለአንድ ሴሚስተር የተሰጠው ትምህርት በማዕከል የጋራ ፈተና ተዘጋጅቶ ለተቋማት እንዲላክ፣ ተቋማት ፈተናውን የማስተዳደር ውጤት የመግለጽና በ2016 ፍሬሽማን ፕሮግራም ለመከታተል ብቁ ሆነው የተገኙት (ማለትም በተቋማት የውስጥ ፈተና 50 ከመቶ፣ በማዕከል የተዘጋጀው ፈተና 50 ከመቶ) ተደምሮ በድምሩ 50 ከመቶና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡቱን እንዲያሳወቁ፣ ይህ አጠቃላይ ሂደት እስከ ሰኔ 30/2015 ድረስ እንዲጠናቀቅ አሳስቧል።

The post የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሐምሌ 19 እስከ 30/2015 በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ይሰጣል first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply