የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የመጀመሪያ ዙር ተፈታኞች ወደ ዩኒቨርስቲዎች በመግባት ላይ ናቸው

ሐሙስ መስከረም 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የ2014 የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለመውሰድ የመጀመሪያ ዙር ተፈታኞች ከዛሬ ጀምሮ ወደ ዩኒቨርስቲዎች በመግባት ላይ እንደሚገኙ ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የፊታችን ሰኞ መስከረም 30 የሚጀምረው እና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጠውን ብሄራዊ ፈተና ለመፈተን ተማሪዎች ወደ ተመደቡባቸው ዩንቨርስቲዎች እየገቡ ሲሆን፤ ተማሪዎቹ በሚገቡበት ተቋም እንዲሁም ከመነሻቸው የፀጥታ አካላት ፍተሻ እያደረጉ ይገኛሉ።

ብሄራዊ ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቀ እንዲሁም የተማሪዎች ደህንነት እና የተቋማት ሰላም እንዲረጋገጥ 8,000 የፌዴራል ፖሊስ እንደሚሳተፉ ተነግሯል።

በተያያዘ ዜና የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ የኦሮሚያ ክልል ትምህር ቢሮ አመራሮች የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለመስጠት ያደረገውን ዝግጅት ጎብኝተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በጉብኝታቸዉም በፕሮግራማቸዉ መሰረት ዛሬ ለፈተና መግባት የጀመሩ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎችን አግኝተዉ አናግረዋል፡፡

ፕ/ር ብርሃኑ በጉብኝታቸውም ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ዩኒቨርሲቲዎች ያደረጉት ዝግጅት አስደሳች መሆኑን በመግለጽ፤ የፈተናውን ደህንነት፣ ያለምንም የፈተና ስርቆትና ኩረጃ ለማካሄድ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን መከናወናቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን እየታየ ያለው ውጤትም አስደሳች መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ዩኒቨርሲቲዎችና የተለያዩ የመንግስት ተቋማት እያደረጉት ያለው ጥረቶች ምን ያህል አቅም እንዳለ የሚያሳይና የሚያስመሰግን መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ አሁን መፈተን ለማይችሉ ተማሪዎች ፈተናውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የእስልምና እምነት ተከታዮች መስከረም 28 የመዉሊድ በዓል አክብረዉ በማግስቱ እሁድ መስከረም 29/2015 ወደ መፈተኛ ዩኒቨርስቲዎች መግባት እንዲችሉ በልዩ ኹኔታ የተፈቀደላቸዉ መሆኑን ማሳወቁ ይታወሳል።

The post የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የመጀመሪያ ዙር ተፈታኞች ወደ ዩኒቨርስቲዎች በመግባት ላይ ናቸው first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply