ረቡዕ ግንቦት 2 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የ2016 የትምህርት ቤት የክፍያ ጭማሪ ከወላጆች ጋር በቂ መግባባት ላይ ሳይደርስ ወደ ተግባር መግባት እንደማይቻል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ለሚገኙ የግል እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ትምህርት ቤቶች በጻፈው ደብዳቤ፤ የ2016 የክፍያ ጭማሪ በተመለከተ በቀን 12/08/2015 ከኹሉም ት/ቤት ባለቤቶች ጋር ባደረግነው ውይይት መሠረት፤ የክፍያ ጭማሪው በት/ቤቱ እና በወላጆች ውይይት እና መግባባት መሠረት ያደረገ እንዲሆን በጋራ መሥማማት ላይ መደረሱን አስታውሷል፡፡
ቢሆንም ግን፤ በከተማዋ አንዳንድ ተቋማት የክፍያ ጭማሪውን በተመለከተ ከወላጆች ጋር በቂ ስምምነት ላይ ያልተደረሰ መሆኑን ባለስልጣኑ በውይይቱ ወቅት በአካል ተገኝቶ ባደረገው ምልከታ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
ስለሆነም በ2016 የትምህር ዘመን የክፍያ ጭማሪ ከወላጆች ጋር በቂ መግባባት ላይ ሳይደርስ ወደ ተግባር መግባት እንደማይቻል ያሳሰበው ባለስልጣኑ፤ ባለው አሰራር መሰረት ከተማሪ ወላጅ ተወካዮች እና ከባለስልጣን መ/ቤቱ ጋር ውይይት በማድረግ በሚቀመጠው የጋራ አቅጣጫ መሰረት ብቻ ወደ ተግባር የሚገባ መሆኑን አሳስቧል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አክሎም፤ የ2016 የተማሪዎች ምዝገባ በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የትምህርት ቢሮ በሚያወጣው የትምህርት ካላንደር መሠረት ከሀምሌ 2015 በኋላ ብቻ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ይህንን ውሳኔ ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
በዚህም መሠረት፤ የየትኛውም ትምህር ቤት ወላጆች ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ዙሪያ ለሚያቀርቡት ቅሬታ፣ እንግልትና ጥቆማ ትምህርት ቤቱ ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑንም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በጥብቅ አሳስቧል።
The post የ2016 የትምህር ቤት ክፍያ ጭማሪ ከወላጆች ጋር በቂ መግባባት ላይ ሳይደርስ ወደ ተግባር መግባት እንደማይቻል ተገለጸ first appeared on Addis Maleda.
Source: Link to the Post