ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የፓርላማ አባል ዛሬ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ

በሃሚድ አወል

በትላንትናው ዕለት ያለመከሰስ መብታቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተነሳው የፓርላማ አባል ዶ/ር ጫላ ዋታ፤ ዛሬ ረቡዕ ረፋድ ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወል ሱልጣን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ዶ/ር ጫላ በፌደራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የተወካዮች ምክር ቤት በትላንትናው ዕለት በነበረው መደበኛ ስብሰባው የፓርላማ አባሉን የህግ ከለላ ያነሳው፤ ዶ/ር ጫላ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት “ከመንግስት ሕግ ውጪ” ግዢዎች እና የፋይናንስ አስተዳደር ጉድለቶችን ለመፈጸማቸው “በቂ አመላካች ሁኔታዎች አሉ” በሚል ነበር። ዶ/ር ጫላ ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ኃላፊነታቸው የተነሱት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ከኃላፊነታቸው የተነሱት፤ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ካካሄደው የስራ ግምገማ በኋላ “በወሰደዉ አስተዳደራዊ እርምጃ መሰረት” መሆኑን የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በወቅቱ አስታውቆ ነበር። ከዘጠኝ ወር በፊት በተወሰደው በዚሁ አስተዳደራዊ እርምጃ፤ የዩኒቨርስቲው ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶችም ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል። 

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የዩኒቨርሲቲውን የ2013 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ይፋ ካደረገ ከሶስት ወራት በኋላ ነው። በ40 ገጾች የተዘጋጀው የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ የሂሳብ ወጪ እና የግዢ ስርዓት ጉድለቶች እንዳሉበት ያመለከተ ነበር።

የዶ/ር ጫላ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የውሳኔ ሃሳብ ለፓርላማ ያቀረበው የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በዚሁ የኦዲት ግኝት ላይ በመመስረት ውሳኔውን እንዳዘጋጀ አስታውቆ ነበር። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ ትላንት ማክሰኞ ለፓርላማ ሲናገሩ “ለዚህ ጉዳይ ትልቁ መነሻ የኦዲት ግኝት ነው” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ይታከልበታል]

The post ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የፓርላማ አባል ዛሬ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply