ያለመከሰስ መብት በሽግግር ፍትህ ሂደቱ ላይ አይሰራም (የፖሊሲው ዋና ይዘቶች)

በመላው አገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆነው የሽግግር ፍትህ ያስፈለገው በተለያዩ ጊዜያት በመንግስት መዋቅሮች እና መንግስታዊ ባልሆኑ ግለሰቦች እና ተቋማዊ ተዋንያን የተፈጸሙ ግጭቶች፣ በደሎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተደጋጋሚ ኡደት በአገረ መንግስቱ ግንባታ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳደሩ እና በዘላቂነት መፈታት የሚገባቸው በመሆኑ ነው።

በጸደቀው የአገሪቱ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ላይ አዲስ ማለዳ እንደተመለከተችው የፖሊሲው ዓላማ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውድ መሰረት ያደረገ፣ የተቀናጀ እና የተናበበ የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚመራበት እና የሚተገበርበትን ሥርዓት በመዘርጋት ዘላቂ ሰላም፣ ዕርቅ፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕ እና ዲሞክራሲ የሚረጋገጥበትን መደላድል መፍጠር እንደሆነ ተገልጿል።

በፖሊሲው መነሻ ሁኔታዎችና አስፈላጊነት ላይ “በኢትዮጵያም ዘመን ለዋጁ በደሎች ፍትሕን ለማረጋገጥ፣ ቁርሾዎችን ለመቀነስ እና የቀጠሉ ግጭቶች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በዘላቂነት ለማስቆም ከምንጊዜውም በላይ ተጠያቂነትን በማስፈን የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለተፈጸሙ በደሎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማውጣት፣ በቅድመ−ሁኔታ ላይ የተመሰረተ የምህረት አሰራር መተግበር፣ ግለሰባዊ እና ማህበረሰባዊ ዕርቅን ማሳለጥ፣ የማካካሻ ሥርዓትን መመስረት፣ እንዲሁም የተቋምና የህግ ማሻሻያ ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ በተጎጂዎች ላይ ያተኮረ የተሟላ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት መተግበር ፍፁም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” ይላል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚደረገው የሽግግር ፍትሕ ሂደት የወንጀል ምርመራ በማካሄድ እና ክስ በመመስረት አጥፊዎች ተጠያቂ
የሚሆኑበትን ሥርዓት የሚዘረጋ ይሆናል። በዚህም
ጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ከባድ ወንጀሎችን መለየት የሚያስችል ግልፅ መለያ መስፈርት ይዘረጋል፤
– በአገሪቱ የወንጀል ሕግ ውስጥ ያልተካተቱ ዓለም-አቀፍ ወንጀሎችን በተመለከት አገሪቱ ከተቀበለቻቸው ዓለም-አቀፍ
ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ይደረጋል፤
– የወንጀል ምርመራ እና ክስ ስራዎችን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር የሚያስችሉ የአሰራር ሥርዓቶች ይዘረጋሉ

ምርመራ የሚከናወንባቸው እና ክስ የሚመሰረትባቸው አጥፊዎችን በተመለከተ በአጥፊዎች ላይ የወንጀል ሙሉ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ያለመከሰስ መብት ተፈፃሚነት እንዳይኖረው ይደረጋል።

ይሁን እንጂ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር በሁሉም አጥፊዎች ላይ ምርመራ ማካሄድ እና ክስ መመስረት ተመራጭ አካሄድ አይሆንም ተብሏል።

ከአጥፊዎቹ ብዛት፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ከሚተገበርበት የጊዜ ወሰን ስፋት፣ በዓለም-አቀፍ ደረጃ ካለው የሽግግር ፍትሕ ተሞክሮ አኳያ፣ እንዲሁም በአጥፊዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እና ክስ ስራዎችን ለማካሄድ ከሚያስፈልገው ረጅም ጊዜ እና ከሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ አንፃር የምርመራ እና ክስ የመመስረት ስራው ትኩረት ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ብቻ እንደሚሆን በፖሊሲው ወስጥ ተገልጿል።

በአገር ውስጥ የማይገኙ ከፍተኛ ደረጃ የወንጀል ተሳትፎ ያላቸው አጥፊዎች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ከሚገኙበት አገር ተላልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ ተገቢ ስራ ይሰራል።

የሽግግር ፍትህ ሂደቱ አሁን ካለው የወንጀል ምርመራ እና ዐቃቤ ህግ ተቋም ውጪ በሆነ ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ራሱን ችሎ የሚቋቋም እና የሕዝብ አመኔታ የሚኖረው አዲስ ልዩ ዐቃቤ ህግ ተቋም እንዲሁም በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ስር በልዩ ችሎት አማካኝነት እንደሚከናወን አዲስ ማለዳ ከፖሊሲው ተመልክታለች።

እውነትን የማፈላለግ፣ ይፋ የማውጣት እና የዕርቅ ተግባራት ከተጽዕኖ እና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ እና ገለልተኛ
ሆኖ በሚቋቋም አዲስ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን አማካኝነት እንደሚከናወን ተገልጿል። በዚህም ምህረት የሚሰጥባቸው እና የማይሰጥባቸው ጉዳዮች እንዲሁም በቅድመ ሁኔታ ላይ ስለሚመሰረቱ ምህረቶች እንዲሁም የማካካሻ ሂደት በፖሊሲው ዝርዝር አሰራር ተቀምጧል።

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው የትግበራ የጊዜ ወሰን ‘የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ከጸደቀበት ከ1987 ጀምሮ’ ካለው ጊዜ በሽግግር ፍትህ ሂደቱ ‘መረጃ እና ማስረጃ እስከተገበት ጊዜ ድረስ’ እንደሚሆን ተመላክቷል።

‘በአገራዊ የሽግግር ፍትሕ ሂደት የማይሸፈኑ ጉዳዮች፣ ጥሰቶች እና ግጭቶችን’ በተመለከተ ለተፈጸሙ በደሎች በመንግስት ደረጃ ይቅርታ መጠየቅ፤ እንዲሁም ባህላዊ የእርቅ ሂደቶችን እና መካካሻዎችን ተፈጻሚ ማድረግ ለክልሎች ከተሰጡ ኃላፊነቶች መካከል ናቸው።

ከመንግስታዊ አካላት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅቶች በሽግግር ፍትህ ሂደቱ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply