ያለምንም የፖለቲካ ልዩነት ለኢትዮጵያ ህልውና በጋራ መቆም አለብን-ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ::

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 24፣2013  ዜጎች ያለምንም የፖለቲካ ልዩነት ለኢትዮጵያ ህልውና በጋራ መቆም እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጥሪ አቀረቡ፡፡ የኢዜማ ፓርቲ  አመራርና አባላት “ደሜን ለእናት ሀገሬ” በሚል መሪ ሃሳብ በብሔራዊ ደምባንክ በመገኘት ደም ለግሰዋል።

የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የደም ልገሳ መርሃ ግብር የተዘጋጀው ፓርቲው ለሀገሩ ህልውና መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያለውን ድጋፍ ለመግለጽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ለህልውና ዘመቻው የቁሳቁስ ድጋፍን ጨምሮ ወደ ግንባር እስከመዝመት የደረሰ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ፓርቲው የአሸባሪው የህወሃት ቡድን በፈጸመው ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች የ250 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉንም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል። የሀገርን ህልውና ማስጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን የሚናገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ከዚህ አኳያ ሁሉም ዜጋ ያለምንም የፖለቲካ ልዩነት ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ በጋራ መቆም እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

የፓርቲው ዋና ጸሀፊ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው የፓርቲው አመራሮች ግንባር ድረስ በመሄድ ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት ማሳየታቸውን አስታውሰዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply