ይድረስ ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ – (ጥብቅ ምሥጢር!) ምሕረት ዘገዬ (አዲስ አበባ)

በመጀመሪያ – ይሄ በስፋት እየተቀነቀነ ያለ የይቅርታና ምሕረት እሳቤ ላይ ያለኝን ቅሬታና አስተያየት ልናገር፡፡ በመሠረቱ ይቅርታም ሆነ ምሕረት እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊም ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ልዩ ትኩረት የሚሰጠው የጽድቅ መንገድ መሆኑ አይካድም፡፡ ይሁንና እነዚህ ጽንሰ ሃሳቦች አላግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ትርጉማቸውን እንዲያጡና የተቀደሰ ዓላማቸውን እንዲስቱ ማድረግ አይገባም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንንም በሚመለከት የሚለው አለው፤ “የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፎ የሚሰጥ በአንገቱ የወፍጮ መጅ ታስሮ ወደ ጥልቁ ባህር ቢወረወር ይሻለዋል” የሚለው ጥቅስ የሚያሳየን ይቅርታና ምሕረት የማይሰጣቸው ወንጀሎችና ኃጢኣቶች መኖራቸውን ነው፡፡ ስለሆነም በደፈናውና በጅምላ የአንድን ከሥር መሠረቱ አሸባሪ የሆነን ቡድን አባላት ይቅርታና ምሕረት በሚል ከወንጀላቸው ነፃ ማድረግ በምሕረትና ይቅርታ መቀለድ ነው፡፡ ለቀጣዩም ሆነ አሁን ላለው ትውልድ የሚያስተላልፈው አሉታዊ መልእክትም መጤን ይገባዋል፡፡ ስለሆነም ለነፃነት የሚከፈለው መስዋዕትነት በሞራልና በምግባር ራስን ወደባዶነት እስኪወስድና በፈሪነት ወይም በታጋሽነት ለትዝብት እስኪዳርግ ድረስ የተጋነነ መሆን የለበትም፡፡ እየተስተዋለ!

በበኩሌ እነዚህን የሕወሓት ወንጀሎች ይቅርታ አደርጋለሁ፡- ሀብት ንብረት ይዝረፉ – ተሠርቶ ይተካል፡፡ በአንድ የሰው ዘር ላይ (በአማራው ላይ) የዘር ማፋት ዐውጀው ግድያና ጭፍጨፋ ይፈጽሙ – ግዴለም፤ በሌሎች ሀገሮች ውስጥም ተፈጽሟል፡፡ ኢትዮጵያን ወርረው ሀብት ንብረቷን በግላጭ ይቆጣጠሩ – ጊዜያቸው ሲደርስና አምላክ ሲፈቅድ ይለቃሉና ይሁን፡፡ ዜጎችን በጥላቻና በበቀል ይሰሩ፤በአግባቡ ያሰቃዩ፤ በአግባቡም ይግደሉ – ሰው የሚጠላውን ማንገላታት ያለና የነበረ ነውና ግዴለም፡፡ ሰዎችን ከመኖሪያና ከቀያቸው ያፈናቅሉ፤ ንግዱንና ፖለቲካውን በብቸኝነት ይዘባነኑበት፤ ሀገር ምድሩን በማይምነት ጥቁር መጋረጃ ይሸፍኑት፤ ግዴለም – ይቅር እላለሁ፡፡ ….

ነገር ግን አንድን ንጹሕ ዜጋ በህግ ስም ወደ “ማረሚያ ቤት” ካስገቡ በኋላ ከሃይማኖትም ከሞራልም ከባህልም እጅግ ባፈነገጠ ሁኔታ ወንድን በወንድ፣ ሴትን በሴት ማስደፈርና ያንንም በፊልም ቀርፆ “ከአሁን በኋላ ከፖለቲካ ካልወጣህ/ሽ ይህን ፊልም አሰራጭተን እናዋርድሃለን/ሻለን!” ብሎ ሰውን በቁም መግደል ከወንጀሎች ሁሉ የከፋና ሰይጣን ራሱም የማያውቀው የወንጀል ዓይነት ነው፡፡ በዚህ የወያኔ ወንጀል አንገታቸውን ሰብረው የሚኖሩና ከፖለቲካው መድረክ እስከወዲያኛው የሸሹ ወንድምና እህቶቻችን ብዙ ናቸው፡፡ ይህን ወንጀል የፈጸሙና ያስፈጸሙ ወያኔዎች እንደልብ የሚዘባነኑባት ኢትዮጵያ አሁን በሕይወት ካለች ለውጥም የለም፤ ነፃነትም ገና አልመጣም፡፡ በይቅርታና ምሕረት ስም  ይህን አስከፊ የሞራል ውድቀት በሀገራችን ያስፋፉ እነዚህ ሰዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ምንም ለውጥ አልመጣም፤ ለውጥ መጣም ከተባለ የውሸትና የማስመሰል ነው፡፡

እኔ ለውጥ መጣ የምለው ሞራላችንን በዚህ መልክ ያንኮታኮቱ ጥቂት ሰይጣኖች – ምናልባት ከመቶና ሁለት መቶ ላይበልጡም ይችላሉ – በሚዲያ ቀርበውና የሠሩትን ተናዘው እውነተኛ ንስሃ ሲገቡ ነው፡፡ አለበለዚያ እኛም አእምሯችን እያመረቀዘ፣ እነሱም ለተጨማሪ ጥቃት አድብተው ጊዜ እየጠበቁ ለውጥና ነፃነት መጣ ብንል ቀልድ ነው፡፡… ይህንን ለነዐቢይ የቤት ሥራ እተዋለሁ፡፡

 

“ዐመል ያወጣል ከመሀል” ይባላል፡፡ ሰሞኑን የምናያት አንጻራዊ የነፃነት አየር የተገኘችው በሁሉም ዜጎች አስተዋፅዖ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሃምሣ በመቶ ያህሉን የድል ውጤት ለለማ ቡድን ብሰጥ አይከፋኝም፡፡ ሌላውን የሃምሣ መቶኛ ድልድል ወደፊት እኔም ሆንኩ ሌሎች ይናገሩታል፡፡  የኦነግ ድርሻ ግን በጣም ትንሽ እንደሆነ ከአሁኑ መናገር እችላለሁ፡፡ ማስረጃየም ትናንት በአዲስ አበባ የተከናወነው አስቂኝና አሳዛኝ ድራማ ነው፡፡ ኦነግ ለውጡን ቢደግፍ ኖሮ ይህን የመሰለ የጅል ሥራ አይሠራም ነበር፡፡ የወለደውን ልጅ አንቆ የሚገድል እምብዝም አልተለመደምና “ኦነግ ይህ ለውጥ እንዲወለድ አስተዋፅዖ አድርጓል” ብዬ እንዳምን የትናንትናው ድርጊት ሊከሰት ባልተገባ፡፡

ኦነጎች ወደ ሀገር ቤት ሊገቡ ነው መባልን ሰምተናል፡፡ ይግቡ ጥሩ ነው፡፡ በባዕድ ሀገር በስደት መኖር ወይም በጥቂት ተዋጊዎች እዚያና እዚህ ጥይት እያጮኹ ዝንታለም ከቀየ ተነጥሎ ሕይወትን መግፋት አሰልቺ ነውና ወደ ሀገር መግባት መልካም ነው፡፡ ይህ ሲሆን ግን ወደ ሀገር እንዲገቡ ዋና ምክንያት የሆኑ የለውጥ ኃይሎችን አመስግኖና በሚቸግራቸው ተጋግዞ በሰላም እንደመግባት “በላይ እንደገዳይ” እንዲሉ የፈነጠቀችዋን ነፃነት ለማዳፈን በባንዲራ ሰበብ ይህን ያህል ሁከት መፍጠር ጤናማነትን አያሳይም – ትልቅ ሞኝነት ነው፡፡ ይህ ነገር በአስቸኳይ ካልታረመ ቤተሰባቸውንና ሕይወታቸውን ሳይቀር መስዋዕት ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ የለውጥ ሐዋርያትን ድካምና ልፋት በዜሮ ማባዛት ነው፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና ሃምሳ ዓመት ተጎልተው ከማርጀት ባለፈ አንድም ለውጥ ሳያመጡ ዛሬ በእግዚአብሔር ረድኤትና በጥቂቶች ልፋት ብልጭ ያለችውን የነፃነት ጮራ ለማጨናገፍ መራወጥ የዕብደት ከመሆኑም ባሻገር ያለንን የሥልጣን ሱስ አመላካች ነውና ወጣቶችን ለእሳት መማገድ አሁኑኑ እንዲቀር የዚህን አስጠሊታ ድራማ ደራሲያንን በግሌ እጠይቃለሁ፡፡

ሕወሓት በጭካኔው በዓለም አንደኛ እንደሆነ ብዙዎቻችን እናምናለን፡፡ ኦነግ ግን ለውድድር እንኳን የማይቀርብ የአንደኞች ሁሉ አንደኛ እንደሆነ በበኩሌ አውቃለሁ፡፡ ብዙ መናገር አያስፈልገኝም፡፡ ጉለሌ አካባቢ ቀደም ሲል በአንድ አባሉ ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ግድያና ወለጋ ውስጥ በጓደኛየ በጃቦ ሲራጅ  ላይ የወሰደው እርምጃ በቂ ምስክሮቼ ናቸው፡፡ ወያኔ በራሷ ሰዎች እርምጃ ስትወስድ በ“ርህራሄ” ነው፡፡ ወያኔ ጭካኔዋ ገደብ የሚያጣው ከጎሣዋ ውጪ ባሉ ምሰሥኪን ዜጎች ላይ ነው፡፡ የኦነግ ጭካኔ ግን ምንጩ ባይገባኝም በገዛ ብሔሩ ሰዎች ሳይቀር እጅግ የከፋ ዐረመኔ ነው፡፡ ሕወሓቶች በጊዜ ሂደትና በትምህርት ወይም በተሞክሮ ጭካኔያቸውን እየሞረዱ የማይሄዱና ይልቁንም ዐረመኔነታው እየጋመና እየጎመራ እንደሚሄድ ሁሉ ኦነግም ልክ እንደዛው ለጭካኔው ለከት የሌለው አድሮ ቃሪያ ድርጅት ነው፡፡ የጭካኔ መሠረት ደግሞ በአብዛኛው የበቀል ጥማትና የደደረ ድንቁር ነው፡፡ ጭካኔ የሚበዛው ሰው አእምሮውን ለመጠቀም ያልታደለና ተፈጥሮው ከእንስሳነት ጠባይም የወረደ ነው፤ ያሳዝናል፡፡ አንድ ሰው ወይም አንድ ድርጅት በጊዜ ሂደት እየተማረና እየሰለጠነ ካልሄደ ደግሞ ከሰውነት ደረጃ የሚያወጣ መሠረታዊ ችግር አለበት ማለት ነው፡፡ ሀገራችን በተደጋጋሚ እየተቀጣች ያለችው እንግዲህ እንዲህ ያሉ ሰዎች የፖለቲካ ልጓሙን ስለሚይዙት ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ይህ አስቀያሚ ጉዞ መገታት ይኖርበታል፡፡

ለማንኛውም የለማ ቡድን ብዙ ትግል ከፊቱ ተደቅኗል፡፡ እነዐቢይ ሲገነቡት የሚውሉትን ሲያፈርሱ የሚያድሩ እስስቶችና ሸለምጥማጦች ሞልተዋል – ከሩቅም ከቅርብም፡፡ መጠንቀቅ ደግሞ የውስጡን ነው – ዱሮም ጠላት ከሩቅ አይመጣምና፡፡ የሚያስጠጋቸውን ወገኖች መመርመር አለበት፡፡ እንዶድ በየዋህነቷ ወንዝ ወስዷታል፡፡ ብዙ ያልጠረጠረ ዜጋም ከየሚኖርበት ተመንጥሯል፡፡ በገንፎ ስንጥር ያለቀውን የዋህ ወገንም መዘንጋት አይገባም፡፡ ያጎረሱትን እጅ የሚነክስ ይሁዳ ሁሉ በሚርመሰመስበት በዚህ የአካይስት ዘመን በስመ ዴሞክራሲና ነፃነት የመጣውን ሁሉ ማግበስበስ ትርፉ ጸጸት ሊሆን እንደሚችል ማስታወስ ተገቢ ነው – ለተወሰነ ጊዜ ወደ ኅዋ ሄዶ የሚመጣ ሰው እንኳን ምን እንደገጠመው እስኪታወቅ በ“quarantine” ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ብቻውን ይቆያል፤ በዚያውም በጥብቅ ይመረመራል፡፡ የበዛ ቸርነትና የዋህነት ለአደጋ ያጋልጣልና “እንደርግብ የዋህ እንደእባብም ልባም ሁን” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ብሂል ማጤን ተገቢ ነው፡፡

“ግምበኞች የናቋት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ሆነች” ይላል ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ – ዛሬ ከመጽሐፍ ቅዱስ አልተላቀቅሁም – ይቅርታ፡፡ ኦህዲድ በወያኔ ጥፍጥፍነቱና ተላላኪነቱ እንደዚያ እንዳልተናቀ ጊዜ ደጉ አሁን አሁን የነፃነት አርበኛ ሊሆን ችሏል፤ መሢሑም ከርሱ ዘንድ ተወልዷል፡፡ ይህን መልካም ጅምሩን ግን ከሌሎች የቀን ጅቦችና ደም አነፍናፊ ዘረኞች ተግቶ ሊጠብቀው ይገባል፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵውያን ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያንና የመላው ዓለም ሕዝብ ንብረት ነች፤ በአዲስ አበባ የመጣ በሰው ልጅ ዘር ዐይን የመጣ ያህል ነው፡፡ ይህችን ከተማ በጨርቆች ቱማታ ማጥለቅለቅና በጨርቅ ምክንያት ሁከት ፈጥሮ የከተማዋን ውበት ማጥፋት ወያኔነትና የወያኔ ተላላኪነት ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ከተናገራቸው ንግግሮቹ የያዝኩለት ቁም ነገር ባንዲራን “ጨርቅ” ማለቱ ነው – መለስን ብዙዎቻችን ስለምንጠላው የሚናገረውን ሁሉ ሳናስተውልና ለማስተዋልም ሳንፈልግ እናበሻቅጥበታለን እንጂ እንደዚያ ማለቱ እውነቱን ነው፡፡ ዋናው ነገር እርሱም እንዳለው ከጨርቁ በስተጀርባ የሚገኘው ነገር ነው፡፡ እንጂ የዓለም ሀገሮች ያሏቸው ባንዲራዎች ሁሉ ከጨርቅ እንጂ ከብረት ወይም ከእንጨት ባለመሠራታቸው ባንዲራ ሁሉ ጨርቅ ነው፡፡

ባንዲራ ከጨርቅነት የሚወጣው ያንዱን አውርዶ የሌላውን በመተካት የተሰቀለውን ማክበር የወረደውን ደግሞ ማቃጠል ወይም እንደተራ ከረጢት ቆጥሮ ጨውና ስኳር መቋጠር ሲጀመር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘርና ብሔር ሳይለይ በጋራ የተዋደቀላትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ለአንድ ብሔር ብቻ በመስጠት በዓለም የታወቅንባትን ይህችን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ መለያችንን ማዋረድ ራስን ማዋረድ ነው – ራስን እንዳለማወቅና እንደማዋረድም ያለ ጅልነት ደግሞ የለም፡፡ ኦሮሞው አፄ ምኒልክ፣ ኦሮሞው አፄ ኃ/ሥላሤ፣ ኦሮሞው መንግሥቱ ኃ/ማርያም፣ ኦሮሞው ጄኔራል ተፈሪ በንቲ፣ ኦሮሞው ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ኦሮሞው ኮሎኔል አብዲሣ አጋ፣ ኦሮሞው ጎበና ዳጨው፣ ኦሮሞው ፊታውራሪ ሀ/ጊዮርጊስ (አባ መላ)፣ ኦሮሞው ጄኔራል ረጋሣ … ስንቱን አንስቼ ስንቱንስ ትቼ… ይሄ ሁሉ ኦሮሞ የተዋደቀላትን ባንዲራ ዛሬ ጊዜ ተቀይሮ ዘፈን ተለውጦ በሳይቸግር ጤፍ ብድር የነዚያ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ልጆች የአባቶቻችንን ሰንደቅ ዓላማ ስናቃጥል የነሱ ዐፅም ምን እንደሚለን ብናውቅ ክፉኛ ባፈርን፡፡ የጠላትን ምክር ሰምቶ የተጠቀመ የለምና በዚህ አሣፋሪ ድርጊት የተጠመዳችሁ ወገኖቼ ብዙም ሳይረፍድባችሁ በቶሎ ወደ አቅላችሁ ተመለሱ፡፡ የጦር ዐውደ ግምባሮችን አታብዙብን፡፡ መንጋቱ ለማይቀረው ሌሊቱን አታርዝሙብን፡፡ የወያኔ ዳረጎት ይቅርባችሁ፤ ካከማቹት የራሳችሁን ሀብት ጥቂቱን መልሰው ለናንተ በመስጠት የጋራ ሀገራችሁን ለማፈራረስ እየተጠቀሙበት ነውና ይቅርባችሁ፡፡ የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን አሁኑኑ ወደኅሊናችሁ ተሰብሰቡ፡፡

ይህ ባንዲራ ላይ የመዝመት አዲስ ፈሊጥ በአንድ መልኩ ሲታይ ያለማወቅና የጠላት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆንን ወይም  የመሠሪዎችን ዒላማ ለማስፈጸም በገንዘብ መገዛትን የሚያመለክት የክፍለ ዘመኑ ትልቅ ክስረት ነው፡፡ ለማንኛውም አዲስ አበባን ለቀቅ አድርጓት፡፡ የፈሰሰው ደም ከበቂ በላይ ነውና ከእንግዲህ መጃጃል ይቁም፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ፡፡

“የዳኛ ልል ያማታል፤ የምንትስ ልል ያፋታል” ይባላል፡፡ መንግሥት መጠንከር አለበት፡፡ መላላት የለበትም፡፡ ልል ከሆነ ይናቃል፤ እጅግ ጥብቅ ከሆነም ይፈራል፡፡ ስለዚህ እንዳይናቅም እንዳይፈራም መሀል መንገዱን ይዞ ውዴታንና ከበሬታን በማግኘት ሀገርን በፍቅርና በሰላም ለማስተዳደር መጣር ይኖርበታል፡፡ ከዚህም በተያያዘ ይህ አገርን እያመሰ የሚገኘውን የመንጋ ፍርድና የቡድን ባንዲራ መከታተልና መቆጣጠር እንዳስፈላጊነቱም የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ይገባዋል፡፡ አቶ ለማ መገርሣ “ባርነትን መሸከም የቻልን ሕዝቦች ነፃነትን መሸከም እንዴት አቃተን?” ብሎ የተናገረው ትክክለኛ ንግግር ሊከነክነን ይገባል፡፡ ባርነት የተፈጥሮ ፀጋችን ይመስል ትንሽ ነፃነትን ስናገኝ እንዲህ መረን የምንለቅ ከሆነ ወያኔን ለመመለስ ደቂቃም አይፈጅም፡፡ ባገር አማን የሕዝብን መለያ ባንዲራ በጠራራ ፀሐይ እያወረዱ የድርጅትን ዓርማ መተካትና የሚቃወምን በገጀራ አንገትን ለመቀንጠስ በጭነት መኪኖች ወጣቶችን በሰላማዊ ከተማዎች ማሰማራት ዕብደት ነው፡፡ “የምታሸንፈውን ምታ ቢሉት ወደሚስቱ ሮጠ” እንደተባለው ወያኔ እየገዛ ሳለ ከጫካ ያልወጣ ድርጅት አሁን ሰላም ሲመጣ በአሮጌ ፕሮፓጋንዳ ወጣቶችን አስክሮ ለረብሻ መልቀቅ የታሰረ ውሻን ፈትቶ መንገደኛ እንደሚያስነክስ ባለጌ አባውራ መሆን ነው፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ ደግነቱ ይህም ያልፋል፡፡ ሲያልፍ ግን ያልተፈለገ ጠባሳ እንዳያኖር ነው መጠንቀቅ፡፡ የሠራዊት ገጌታ እግዚአብሔር ከዕብድ ውሾች ሀገራችንንና እኛን ዜጎቿን ይጠብቀን፡፡ አሜን፡፡

Leave a Reply